የአፍሪካ ኅብረት የቡድን 20 ሀገራት አባል እንዲሆን ሕንድ ጠየቀች
አዲስ አበባ፣ሰኔ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የአፍሪካ ኅብረት የቡድን 20 አባል ሀገራትን እንዲቀላቀል የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሙዲ ጥያቄ አቀረቡ፡፡
ናሬንድራ ሙዲ ÷ ለአባል ሀገራቱ መሪዎች በደብዳቤ ጥያቄያቸውን ያስገቡት ሀገራቸው ሕንድ ከሦስት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የቡድን 20 አባል ሀገራትን ጉባዔ በመዲናዋ ኒውደልሂ ልታዘጋጅ ባለበት ወቅት ነው፡፡
ይህ ሐሳብ የመነጨው በዚህ ዓመት በፈረንጆቹ ጥር ወር ላይ በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ከተካሄደው ‘የዓለም አቀፉ የደቡብ ድምፅ’ የመሪዎች ጉባዔ በኋላ ሳይሆን እንዳልቀረ ምንጮች እየጠቀሱ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
እንደሚታወሰው በጉባዔው ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ተሳትፈዋል፡፡
ዘ ኢንዲያን ኤክስፕረስ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ÷ የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሙዲ በደብዳቤያቸው የጠየቁት ኒውደልሂ በሚዘጋጀው የአባል ሀገራቱ ጉባዔ ላይ የአፍሪካ ኅብረት ሙሉ አባል ሆኖ እንዲሳተፍ ነው፡፡
የቡድን 20 የአባልነት ጥያቄ ተቀባይነት የሚያገኘው 20ውም አባል ሀገራት በጉዳዩ ላይ ሲስማሙ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት በቡድን 20 አባል ሀገራት ዘንድ ተቀባይነት ካገኘ ቡድኑ “የቡድን 21 አባል ሀገራት” እየተባለ ሊጠራ ይችላል፡፡
እስከ አሁን ከአፍሪካ አኅጉር የቡድን 20 አባል ሀገራትን የተቀላቀለችው ደቡብ አፍሪካ ብቻ መሆኗ ይታወቃል፡፡