Fana: At a Speed of Life!

በምዕራብ ኦሞ ዞን ከ22 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ሰኔ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲበደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በምዕራብ ኦሞ ዞን ከ22 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቋል፡፡

የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ በአርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ የድርቅ መቋቋምና ዘላቂ የአርብቶ አደር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አማካኝነት መገንባቱ ተገልጿል፡፡

ከ4ሺህ 300 በላይ አርብቶ አደር የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ነው የተመላከተው፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ሃላፊው አቶ ፋጂዮ ሳፒ÷ በክልሉ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ድጋፍና ክትትሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የአርብቶ አደርና ቆላማ አካባዎች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምሩ ቦኒ በበኩላቸው÷ የድርቅ መቋቋምና ዘላቂ የአርብቶ አደር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የአርብቶ አደሩን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ፣የአኗኗር ዘይቤን በማሻሻልና የማህበረሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

የምዕራብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ምትኩ ታምሩ÷ በአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር በመኖሩ በውሃ ወለድ በሽታ በርካታ ህጻናት ለህመም እንደሚጋለጡ አንስተው የተመረቀው የንጹህ ውሃ ፕሮጀክት ይህንን ችግር ለማቃለል ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በተስፋዬ ምሬሳ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.