Fana: At a Speed of Life!

በፌደራልና በክልል መንግስታት መካከል ግንኙነት ማጠናከር ችላ የሚባል ጉዳይ አይደለም – አቶ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፣ሰኔ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፌደራልና በክልል መንግስታት እንዲሁም በራሳቸው በክልሎች መካከል የሚደረገውን የመንግስታት ግንኙነት ማጠናከር በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ችላ የሚባል ጉዳይ አይደለም ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የክልሎች የጋራ ምክክር መድረክ መካሄድ ጀምሯል።

ምክክሩ ፌደራሊዝምን መሰረት ያደረገ የውስጥ መንግስታትን ግንኙነት ማስገንዘብ፣ በፌደራል እና በክልል መንግስታት እንዲሁም ቢሮዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ማሳየት እና ትክክለኛ ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ ተግባራዊ እንዲሆን መንገዶችን ማሳየት አላማ ያደረገ ነው።

በመድረኩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በፌዴራላዊ ስርዓተ-መንግስት ውስጥ በመንግስታት መካከል የሚካሄዱ የእርስ በርስ ምክክሮችና የትብብር ስምምነቶች ከፌዴራል ስርዓቱ ባህርይ የሚመነጭ ነው ብለዋል፡፡

ይህም በመንግስታቱ መካከል ሊከሰቱ የሚችሉ አለመግባባቶችን ለማስቀረት እና ግጭቶች ተከስተው ሲገኙ ተነጋግሮ ለመፍታት ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች እና እቅዶች እንዲናበቡና በሁሉም ክልሎች ተቀራራቢ አፈፃፀም እንዲኖር ለማድረግ ያግዛል ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም ለስርዓቱ ዘለቄታ ተፈላጊ የሆኑ የጋራ አስተሳሰቦችን በመያዝና በማጠናከር በየጊዜው እየጎለበተ የሚሄድበትን አሰራር ለመዘርጋት ወሳኝ መሳሪያ ተደርጎ እንደሚወሰድም አንስተዋል።

“በዚህም መሰረት በፌደራልና በክልል መንግስታት እንዲሁም በክልሎች መካከል የሚደረገውን የመንግስታት ግንኙነት ማጠናከር በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ችላ የሚባል ጉዳይ አይደለም” ሲሉ ገልጸዋል።

በቀጣይም የፌዴራል እና የክልል መንግስታት የነበራቸውን ግንኙነት እና የተጀመሩ ተግባራትን ይበልጥ በማጠናከር በአዋጅ ተዘርዝረው በተሰጡ ተግባራት ላይ ምክክር በማድረግ አሁን ያለውን የአፈጻጸም ደረጃ መገንዘብ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

የጋራ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ግንዛቤ በመያዝ የተጀመረውን የግንኙነት ፎረም ይበልጥ በማጠናከር የጋራ ሀገራዊ ሃላፊነቶችን መወጣት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎችን ጨምሮ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እንዲሁም የፌደራል ሚኒስትሮችና የክልል ቢሮ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.