Fana: At a Speed of Life!

የገቢዎች ሚኒስቴር በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ183 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ሚያዝያ 20፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ183 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዘጠኝ ወራት 190 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 183 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 96 በመቶ  ማሳካቱን ገልጿል፡፡

አፈፃፀሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ37 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወይም የ25 ነጥብ 6 በመቶ እድገት ማሳየቱም ነው የተገለጸው።

የገቢዎች ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማ በቪዲዮ ኮንፈረንስ በአካሄደበት ወቅት ሚኒስትሩ አቶ ላቀ አያሌው ÷ ተቋሙ የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ይህንን አፈፃፀም ለማስመዝገብ ባለፉት ዓመታት ከተገኙ ስኬቶችና ከታዩ ክፍተቶች ልምድ በመውሰድ  የተሻለ ዉጤት ለማስመዝገብ ቆርጦ ወደ ስራ በመግባቱ ነው ብለዋል፡፡

ሚኒስቴር መ/ቤቱ በበጀት ዓመቱ የነበረዉን የላቀ አፈፃፀም በማስቀጠል በቀሪው ወራት አፈፃፀሙን ከፍ ለማድረግ ከመንግስት የተሰጠዉን እቅድ ለማሳካት የነበረው የዝግጅት ስራዎችን አጠናክሮ   ይቀጥላል  ነው ያሉት

ስለሆነም የገቢ አሰባሰቡን ስራ ለማሳካት ለባለድርሻ አካላትና ለግብር ከፋዩ ማህበረሰብ እዉቅና የመስጠት፣ ግብር ከፋዮችንና ሰራተኞችን አወያይቶ የማዘጋጀት ስራ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡

የሚኒስቴሩ የስትራቴጂክ እቅድ ፕላንና ፕሮጀክት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ታደሰ በበኩላቸው ÷ በሀገራችን ብሎም በአለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለመሰብሰብ ያቀደው ገቢ በተፈለገው ሁኔታ እንዳልተሳካና አፈፃፀሙ እንደ ከዚህ በፊቱ ከዕቅድ በላይ ለመሰብሰብ እንቅፋት እንደሆነ አንስተዋል፡፡

ሃላፊው አያይዘውም ከገቢ ድርሻ አንጻር በዘጠኝ ወራት የሀገር ውስጥ ታክስ 100 ነጥብ 67 ቢሊየን ብር፣ የጉምሩክ ኮምሽን 82 ነጥብ 44 ቢሊየን ብር ድርሻ የነበራቸው ሲሆን ከብሄራዊ ሎተሪ ደግሞ 139 ነጥብ59 ሚሊየን ብር ድርሻ አለው ብለዋል፡፡

በተደረገው የስራ ግምገማ ላይ እንደክፍተት ከታዩት ውስጥ በሀገራችን የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ገቢው በተፈለገ መጠን አለመሰብሰቡ፣ የደረሰኝ አጠቃቀም ችግሮች መሆናቸው ተመላክቷል።

ከዚያም ባለፈ ግብር ከፋዮች በወሩ መጨረሻ ላይ ያለውን መጨናነቅና ከወቅቱ ጋር በተያያዘ ወደ ሚ/ር መ/ቤቱ በአካል መምጣት ሳያስፈልጋቸው በየትኛውም ቦታ ሆነው የኢ-ታክስ ቴክኖሎጂን በመጠቀም አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ የተፈጠረ ቢሆንም አገልግሎቱን መጠቀም ላይ ክፍተት እንዳለ እንዲሁም ከዚህ ጋር በተያያዘ የሲስተም ችግር መኖሩና ሌሎች ምክንያቶችም ተነስቷል፡፡

በቀጣይ በተለይም ከገቢ አሰባሰብ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ክፍተቶች ላይ አጠናክሮ መስራት እንደሚያስፈልግና ለዚህም አመራሩ ቁርጠኛ አቋም መውሰድ እንዳለበት አቅጣጫ  መቀመጡም ነው የተገለጸው።

የገቢዎች ሚኒስቴር  በበጀት ዓመቱ 270.2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.