በኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ያጠናውየማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ የመረጃ ስርጭት ሀገራዊ ሪፖርት ይፋ ሆኗል ።
ከታኅሣሥ 2014 ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ 2015 ዓ.ም÷ በፌስቡክ፣ ቲዊተር፣ ዩቲዪብ ፣ ኢንስታግራም እና ቲክቶክ የተሰራጩ የጥላቻ ንግግር እና የሀሰተኛ መረጃዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ነው የዳሰሳ ጥናቱ የተሠራው፡፡
የጥላቻና የሀሰተኛ ንግግሮች በምስል፣ በቪዲዮ፣ በድምፅ እና በጽሑፍ መሰራጨታቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
ፖለቲካ፣ ብሔር፣ ሃይማኖት እና አካል ጉዳትን እንዲሁም ፆታን መሰረት ያደረጉ መሆናቸው እና በፌስቡክ እና ቴሌግራም በጽሑፍ መሠራጨታቸውም በጥናቱ ተመልክቷል፡፡
በተጨማሪም ÷ በዩቲዩብ እና ቲክቶክ ለሀሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር ቪዲዮ ጥቅም ላይ መዋሉም ተጠቁሟል፡፡
በተለይም በዩቲዩብ ፣ ፌስቡክ እና ቲክቶክ የጥላቻ ንግግሮችን ለማሰራጨት የጭካኔ አገላለፅ ዘዴን ሲጠቀሙ÷ ቀሪዎቹ የዋልታረገጥ አገላለፅን ስለመጠቀማቸው ተመላክቷል፡፡
ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎችም የጥላቻ ንግግሮች እና ሀሰተኛ መረጃዎች ምንጭ ሆነዋል ተብሏል፡፡
የማህበራዊ ሚዲያ ተቋማት ላይ ርምጃ ባለመወሰዱም ጉዳዩን አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዳደረሰውም ነው የተገለጸው፡፡
ችግሩን ለመከላከል ያስችል ዘንድም በ2012 የተደነገገውን የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ለማስፈፀም የሚረዳ ደንብ ሊዘጋጅ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
ለዚህም ሁሉን አቀፍ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ነው በሪፖርቱ የተብራራው፡፡
በፀጋዬ ወንድወሰን