Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞችና ተቀባዮች ከአጋር ድርጅቶች ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አጋር ድርጅቶች እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ስደተኞችና የተቀባይ ማህበረሰብ እየገጠማቸው ያለውን ችግር ለማቃለል አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ፡፡

የዓለም የስደተኞች ቀን “ተስፋ ከአገር ባሻገር”በሚል መሪ ሀሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በሚገኝበት በአፋር ክልል አይሳኢታ ከተማ እየተከበረ ነው።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ ያላ፣ የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሊ መመመድ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞ ኮሚሽን(ዩኤንኤችሲአር)ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ ማርጋሬት አቲዬኖን ጨምሮ የመንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ ያላ በዚህ ጊዜ እንዳሉት÷ ቀውስ በበዛበት ዓለም ውስጥ ቁጥሩ እየጨመረ የመጣውን የስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂ ዜጎችን ለማስተናገድ የባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ ያሻል፡፡

በዓለም ላይ ከ100 ሚሊየን በላይ ዜጎች በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሳቢያ ከአገራቸው መሰደዳቸውን ገልፀው፤ ኢትዮጵያም ከ1 ሚሊየን በላይ ስደተኞችን ተቀብላ ሁለንተናዊ ድጋፍ እያቀረበች መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ባላት ውስን ሀብት ከስራ አጥነት ቁጥር ማደግ፣ የሸቀጦች ዋጋ መናር ጋር ተዳምሮ ስደተኞችን በአግባቡ ማስተናገድ ላይ ጉልህ ተፅዕኖ እየፈጠረ መሆኑ መመላከቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የዓለም አቀፍ ድጋፎች መጠን እየቀነሰና እየተቋረጠ መምጣቱ ደግሞ በስደተኞችና በተቀባዩ ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ስጋት መደቀኑን ጠቁመው የነበሩ ድጋፎች ሊጠናከሩ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በዚህም በስደተኞች ዙሪያ ሰብዓዊ ኃላፊነትን የመጋራት ዓለም አቀፍ መርህ መሰረት አስፈላጊውን ሰብዓዊ ድጋፍ እና የጋራ ልማት ፕሮጀክቶችን ትግበራ እንዲያጠናክር አቶ ያዕቆብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.