በክልሉ በርካታ የመልማት ጥያቄዎች ስላሉ ድጋፍ ያስፈልጋል -ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሕዝቦች የመልማት ጥያቄዎች ስላሉ የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ድጋፍ እንዲደረግ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ጠየቁ፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በክልሉ ያደረገውን የመስክ ምልከታ ማጠቃለያ የክልሉ ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ገምግሟል።
የመንግሥትና የሕዝብ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ጥያቄዎችን መመለስ የሚችል ተቋማዊ አሠራሮችን ለመዘርጋት ሲሠሩ መቆየታቸውን ነጋሽ ዶ/ር ኢ/ር)አብራርተዋል።
ክልሉ ሰፊ የሕዝቦች የመልማት ጥያቄዎች ያለበት መሆኑን አስገንዝበው÷ የክልሉን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ የበጀት ቀመር ባለመዘርጋቱ በሥራዎች ላይ ክፍተት ማሳደሩን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
በርካታ ዓመታትን ያስቆጠሩ የፌደራልና በቀድሞ ክልል ተጀምሮ ያልተጠናቀቁ የመንገድ መሠረተ ልማቶችና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚፈልጉ ከክልሉ አቅም በላይ ናቸው ብለዋል፡፡
ለዚህም የፌደራል መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንዲያደርግ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ መጤቃቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
በሌላ በኩል በክልሉ ያለውን ሀብት ወደ ኢኮኖሚ ለመቀየር እንዲቻል አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲቋቋሙ ከሚመለከተው አካል አቅጣጫ ሊቀመጥ ይገባል ብለዋል፡፡
የክልሉ ያለውን ውስን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም የበጀትና የፋይናንስ ሥርዓትን የዘረጋበት አሠራር የሚበረታታ መሆኑን የቋሚ ኮሜቴው አባላት ገልጸዋል፡፡
የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።