Fana: At a Speed of Life!

አቶ ርስቱ ይርዳ ምርጫው በሠላም እንዲጠናቀቅ ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ምሥጋና አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ በወላይታ ዞን የተካሔደው ዳግም የሕዝበ ውሳኔ ምርጫ በሠላም እንዲጠናቀቅ ድጋፍ ያደረጉ አካላትን አመሠገኑ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው ÷ የሕዝበ ውሳኔው አጠቃላይ ሂደት ውጤታማ እንዲሆን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የባለድርሻ አካላትን መድረክ አዘጋጅቶ ከማወያየት ጀምሮ ምርጫ አሥፈፃሚ አካላትን መልምሎ በማሠልጠን አሥፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን አቅርቧል ብለዋል።

አቶ ርስቱ ÷ የሕዝበ ውሳኔ ምርጫው ሠላማዊ ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ተዓማኒ እንዲሆን የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የፀጥታ አካላት እንዲሁም በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮችና ለወላይታ ሕዝብም ምሥጋና አቅርበዋል።

በዳግም ሕዝበ ውሳኔ ምርጫ ድምፅ መስጫ ዕለትም የቦርዱ ሰብሳቢ ብርትኳን ሚደቅሳ በሥፍራው በመገኘት የሕዝቡን የድምፅ አሠጣጥ በመከታተልና በመደገፍ ሂደቱ ሠላማዊ እንዲንሆን የላቀ አስተዋጽዖ ማበርከታቸውን አውስተዋል።

በመሆኑም ሕዝበ ውሳኔው በተሳካ መንገድ እንዲካሔድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አመራሮችና ምርጫ አሥፈፃሚዎች ፣ ለጸጥታ አካላት፣ በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች ፣ በተለይም ለተከበረው የወላይታ ሕዝብ ምሥጋናዬ ይድረሳችሁ ብለዋል፡፡

የሕዝበ ውሳኔው ውጤት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ እንደሚሆን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ሕዝባዊ አንድነትን ሊያጠናክሩ የሚችሉ የጋራ እሴቶቻችንን ማስቀጠል አለብን ሲሉም ነው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት።

በክልል መደራጀት ዋነኛ ዓላማው ለሕዝቡ መንግስታዊ አገልግሎትን በቅርበት ተደራሽ ማድረግ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ ከሕዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ ሂደት በኋላ ኅብረተሰቡ በመደበኛ የልማት ሥራው ላይ ማተኮር እንዳለበት ጠቁመዋል።

በክልል መደራጀት አስተዳደራዊ ወሰን እንጂ በሕዝቦች መካከል ድንበር ማበጀት አለመሆኑን ጠቁመዋል።

የመንግስት ዋነኛ ትኩረት መላውን ሕዝብ ከድኅነት በማውጣት ሁለንተናዊ ብልፅግና እንዲረጋገጥ ማድረግ ነው ያሉት አቶ ርስቱ ፥ ለዚህም የሁሉንም አካላት ጥረትና ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.