በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ “የቤተሰብ የውጪ ምንዛሬ መላኪያ ቀን” ተከበረ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፍ “የቤተሰብ የውጪ ምንዛሬ መላኪያ ቀን” በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ተከብሯል።
መርሐ ግብሩን ያዘጋጁት÷ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት (ጂአይዜድ) እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ነው።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እንድሪስ (ዶ/ር)፣ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሳንዶካን ደበበ፣ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የዳያስፖራ ማህበራት እና አደረጃጀቶች ተወካዮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመርሐ ግብሩ ተገኝተዋል።
በመድረኩ ለቤተሰብ የሚላክ የውጪ ምንዛሬ የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል እና የድህነት ቅነሳ ላይ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ላይ ትኩረት መደረጉ ተመላክቷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ለቤተሰብ የሚላክ የውጪ ምንዛሪ የቤተሰቦችን ሕይወት ከመቀየር ባሻገር ለአገር እድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ እንዲሁም በዲጂታል ቴክኖሎጂ የውጪ ምንዛሪን ለመላክ ያሉ አማራጮችና እድሎች የሚያሳዩ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በተለያዩ የዓለም አገራት ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጪ ምንዛሬን በመደበኛ አማራጮች በመላክ እያበረከቱት ያለውን የዜግነት ኃላፊነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀርቧል።
በ2015 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በሕጋዊ መንገድ ከውጭ አገራት 3 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር (ሬሚታንስ) ወደ አገር ውስጥ መላኩን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ 4 ቢሊየን ዶላር ከሬሚታንስ ለማግኘት በዕቅድ መያዙም ተጠቁሟል።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!