በ“መደመር ትውልድ” የመጽሐፍ ሽያጭ በሚገነባው ሙዚየም ዲዛይን ላይ ውይይት ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ“መደመር ትውልድ” የመጽሐፍ ሽያጭ ገቢ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚገነባው የሙዚየም ግንባታ ዲዛይን ላይ ውይይት ተካሄደ፡፡
ተዘጋጅቶ ለውይይት በቀረበው ዲዛይን ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፣ የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳድር ጌታሁን አብዲሳ እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት መክረዋል፡፡
በውይይታቸውም ሊሠራ የታሰበው ሙዚየም ክልሉን በትክክል ሊገልጽ እንደሚገባ በአፅንዖት መግለጻቸውን የርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
በዚህም መሰረት ክልሉ የሕዳሴ ግድብ መገኛ እንደመሆኑ መጠን ግድቡን ሊገልጽ የሚችል፣ የክልሉን ብሔረሰቦች ባሕል በትክክል ሊያንፀባርቅ በሚችል እንዲሁም በክልሉ የሚገኙ የማዕድን ሐብቶችና ሌሎች ፀጋዎችን በሚያሳይ ደረጃ ግብዓት ተጨምሮበት ተሻሽሎ እንዲቀርብ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡