ሰውን እንደ እቃ መነገድና በሕገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ሲበዛ ጨካኝ፣ አሳፋሪ እና ኢሰብአዊ ወንጀል ነው- ወ/ሮ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 20፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሰውን እንደ እቃ መነገድና በሕገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ሲበዛ ጨካኝ፣ አሳፋሪ እና ኢሰብአዊ ወንጀል ነው ሲሉ ጠቅላይ ዐቃቤ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ አዳነች አቤቤ በፌስቡክ ገጻቸው እንደገለጹት÷ በአለማችን በዚህ ወንጅል የተሰማሩ በአመት ከ150 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያገኙበታልም ነው ያሉት።
ዛሬ የኮቪድ19 ችግር በተከሰተበት ወቅት ዜጎቻችን እንደ እቃ ተጭነው ሲመለሱልን የላኳቸው ወንጀለኞች ግን አሁንም ለገንዘባቸው እንጂ ለሰው አያሰቡም ብለዋል።
ደሃዉን እየደለሉና እየሸጡ ሃብታቸዉን ያሳደጋሉም ሲሉ ገልጸዋል።
ከዚህ አፀያፊ ወንጅል ኢትዮጵያን እና እትዮጵያዊያንን ለመጠበቅ፣ በሰው የመነገድ እና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 1178/2012) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ በነጋሪት ጋዜጣ መታተሙን ተናግረዋል።
አያይዘውም ከህግ ጋር ተባብረን ይህን አፀያፊ ወንጀል ከሀገራችን እናጥፋ በማለት በአጽንኦት ገልጸዋል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!