ተመድ በሰሜን-ምሥራቅ ናይጄሪያ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለማድረስ 20 ሚሊየን ዶላር መደበ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ተመድ በሰሜን-ምሥራቅ ናይጄሪያ አስቸኳይ የምግብ እና የአልሚ ንጥረ-ነገር ድጋፍ ለማድረስ 20 ሚሊየን ዶላር መደበ፡፡
9 ሚሊየን ዶላሩ ከማዕከላዊ የአደጋ ጊዜ ምላሽ የሚገኝ ፈንድ ሲሆን 11 ሚሊየን ዶላሩ ደግሞ ከናይጄሪያ የሰብዓዊ ፈንድ የሚገኝ ነው ተብሏል፡፡
የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ምክትል ቃል አቀባይ ፋርሃን ሃቅ ÷ ረሃብ በተከሰተባቸው የቦርኖ ፣ አዳማዋ እና ዮቤ አካባቢዎች በመንግስት የተመራ ድጋፍ እንደሚቀርብ አመላክተዋል፡፡
ድጋፉ ያለቀላቸው ምግቦች ፣ ንጹህ ውሃ ፣ የጤና እንክብካቤ እና የግብርና ድጋፍ ያካትታል መባሉን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል።
በአካባቢው ወደ 700 ሺህ የሚጠጉ ከ5 ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት ለሕይወት አስጊ በሆነ ከባድ የምግብ እጥረት ሊያጋጥማቸው ይችላል ተብሏል፡፡
ከ500 ሺህ በላይ ሰዎች ከፈረንጆቹ ሠኔ እስከ ነኀሤ ባለው ጊዜ ውስጥ የምግብ እጦት ሊያጋጥማቸው እንደሚችልም የሰብዓዊ አጋሮች ሪፖርት ያመላክታል።
በዚህ ዓመት ለናይጄሪያ ከተያዘው 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር የሰብዓዊ አቅርቦት ድጋፍ እስካሁን 26 በመቶው ብቻ መደጎሙን ቃል አቀባዩ ጨምረው አስታውቀዋል።