Fana: At a Speed of Life!

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከድሬዳዋ ነዋሪዎች ጋር እመከረ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ጋር እመከረ ነው፡፡

በመድረኩ የተገኙት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር ሙሃሙድ ድሪር፥ በኢትዮጵያ የሚታዩ አለመግባባቶችን በምክክር ለመፍታት መሰል መድረኮች አስፈላጊ ናቸው ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክሩም በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል ለሚሉ አካላት ግልጽ እድል እንደሚፈጥር ነው የተናገሩት።

በፖለቲካዊና ማህበራዊ ዘርፎች የሰፉ ልዩነቶችን ለማጥበብ ሀገራዊ ምክክሩ የጎላ ፋይዳ እንዳለውም አስረድተዋል፡፡

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በበኩላቸው ÷ ሀገራዊ ምክክሩ በመንግስትና በሕዝብ መካከል መግባባትን ለመፍጠር ያስችላል ነው ያሉት።

በመድረኩ በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር ድሬዳዋን የሚወክሉ አካላት ይመረጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ወክለው በምክክሩ ለሚሳተፉ ተወካዮች የተዘጋጀ መድረክ በቦንጋ ከተማ እያካሄደ ነው፡፡

ኮሚሽኑ በዛሬው ውሎው በካፋ ዞን በቀጣይ በሀገራዊ የምክክሩ ሂደት ላይ ይሳተፋሉ ብሎ ከለያቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በየወረዳው ተወካዮችን የማስመረጥ (የማስወከል) ስራን እንደሚሠራ ተገልጿል።

ልየታው የሚከናወነው በክልሉ የካፋ ዞን ሶስት ወረዳዎች ከተውጣጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ሲሆን በሂደቱም በኮሚሽኑ የተመረጡ ተባባሪ አካላት ለኮሚሽኑ እገዛ እንደሚያደርጉ በመድረኩ ተነግሯል።

በቀጣይ ተከታታይ ቀናት ከተቀሩት የዞኑ ወረዳዎች ከተወከሉ የማህበረሰብ ክፍሎች የአጀንዳ አቅራቢ ልየታ ይደረጋል ተብሏል።

በዛሬው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መድረክ የአዲዮ፣ ሳይለም እና ጊምቦ ወረዳ የማህበረሰብ ተወካዮች እየተሳተፉ መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

በእዮናዳብ አንዱዓለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.