Fana: At a Speed of Life!

በሶማሌ ክልል 30 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማምረት ዝግጅት እየተደረገ ነው- አቶ ኢብራሂም ዑስማን

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል በዘንድሮው የምርት ዘመን 30 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማምረት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ዑስማን ገለጹ።

አቶ ኢብራሂም ዑስማን÷ በክልሉ የዝናብ ስርጭቱ ዘንድሮ የተስተካከለ በመሆኑ የግብርና ልማት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በመሆኑም በመደበኛ የመኸር እና የበጋ ወቅት በማልማት የተሻለ ምርት ለማግኘት የዝግጅት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ነው የገለጹት።

በክልሉ በዘንድሮው የምርት ዘመን በ1 ሚሊየን ሄክታር መሬት 30 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማምረት ተዘጋጅተናል ብለዋል።

በስንዴ ምርታማነት 200 ሺህ ሄክታር መሬት ለማረስ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመው÷ ከዚህ በፊት በክልሉ የሰብል ልማት ላይ ያልነበረ አዲስ ታሪክ የተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተጀመረው የሌማት ቱሩፋት ንቅናቄ በክልሉ የሚገኘውን ከፍተኛ የእንስሳት ሃብት በዘመናዊ መንገድ ጥቅም ላይ ለማዋል መልካም አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።

በክልሉ የአርብቶ አደሩን ህይወት ማሻሻል የሚያስችል ዘመናዊ የልማት ፖሊሲ ተግባራዊ መደረጉንም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

የድርቅ አደጋን ምላሽ ለመስጠትም ቀጣይነት ያለው የቅድመ ማስጠንቀቂያና ዘመናዊ የእንስሳት ሃብት ልማት አስተዳደር እንዲኖር እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በድርቅ ተጎጂ በመሆኑን በተለዩ ወረዳዎች የእንስሳት መኖ ልማት እና የውሃ አቅርቦትን ለማሻሻል የሚያስችሉ የልማት ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.