Fana: At a Speed of Life!

የቤት ግብር ማሻሻያው የቤት ኪራይ ለመጨመር ምክንያት አይሆንም – የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተግባራዊ የተደረገው የቤት ግብር ማሻሻያ በጥናት ላይ ተመስርቶ የተከናወነ በመሆኑ የቤት ኪራይ ለመጨመር ምክንያት ሊሆን እንደማይችል የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ገለጸ፡፡

ማሻሻያው የከተማ አስተዳደሩ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሰራቸውን ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች እና መሰረተ ልማቶችን ይበልጥ ለማስፋፋት የሚያግዝ ነው ተብሏል፡፡

በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የታክስ ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዘገየ በላይነህ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የቤት ግብር ማሻሻያ ወቅቱን የዋጀ እና ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡

የከተማ ቦታ ኪራይ እና የከተማ ቤት ግብር በሚል በ1937 ዓ.ም የወጣው አዋጅ ለመጨረሻ ጊዜ የተሻሻለው በ1968 ዓ.ም ነው፡፡

አዋጅ ቁጥር 80/1968 ላለፉት 47 ዓመታት በስራ ላይ የቆየ ሲሆን የአዋጁ አንቀፅ አምስት፤ በከተሞች የሚገኙ ቤቶች ባለቤት የሆኑ ግለሰቦች፣ ቤተሰቦች፣ ድርጅቶች፣ ወይም ህብረት ስራ ማህበራት ባለቤት በሆኑበት ቤት ላይ ግብር ወይም ታክስ መክፈል እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡

ከአራት አስርት ዓመታት በላይ ሳይሻሻል የቆየው ይህ አዋጅ የቤት ግብር በየጊዜው እንደሚሻሻል እና ወቅታዊነቱን እንደሚያመላክት አቶ ዘገዬ ተናግረዋል።

በዚህ መሰረት ለረጅም ዓመታት ሳይሻሻል የቆየውን የቤት ግብር ተመን ላይ በጥናት ላይ የተመሰረተ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ ውስጥ የቤት ግብር የሚከፍሉት አብዛኛዎቹ ነባር ይዞታዎች እንደነበሩ አስታውሰው÷ በአዲሱ ጥናት መሰረት የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ ቤቶች የቤት ግብር እንዲከፍሉ መወሰኑንም ነው የገለጹት።

ከዚህ ቀደም የቤት ግብር ሲከፍሉ ከነበሩት ውስጥ ከ22 ሺህ በላይ የሚሆኑት ከ10 ብር በታች እና ከ2 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከአንድ ብር በታች ግብር ሲከፍሉ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

ይህም የህዝቡን አሁናዊ የልማት ጥያቄ ለመመለስ መሰብሰብ ከሚገባው ገቢ አንጻር እጅግ አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሁን የተደረገው ማሻሻያም የቤቶችን ደረጃ፣ መንግስት ለመሰረተ ልማት ያወጣውን ወጪ እና አካባቢያዊ ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ ተመጣጣኝ ግብር እንዲከፈል የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

መንግስት የግብር ከፋዩን ጫና ለመቀነስ በማሰብም ግለሰቦች መክፈል ከነበረባቸው 50 በመቶ እንዲሁም ድርጅቶች 75 በመቶ ብቻ እንዲከፍሉ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

አስተዳደሩ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በርካታ የመሰረተ ልማቶችን መገንባቱንም ነው የገለጹት፡፡

ለአብነትም የተማሪዎች ምገባ፣ መሰረተ ልማቶችን እንዲሁም በርካታ የምገባ ማዕካላትን በመክፈት ህዝቡን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቤት ግብር ማሻሻያውም አስተዳደሩ ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመራቸውን የልማት ስራዎች ይበልጥ ለማስፋፋት የሚውል ገቢ ለመሰብሰብ ሲባል በፍትሐዊነት የተወሰነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በትናትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ የጣሪያ እና ግድግዳ ግብርን ምክንያት በማድረግ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ዋጋ መጨመርም ሆነ ተከራይ ማስወጣት እንደማይቻል መወሰኑ ይታወቃል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.