Fana: At a Speed of Life!

እየጣለ ያለው ዝናብ በተወሰኑ አከባቢዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የብሄራዊ ሜትሮለጂ ኤጀንሲ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአብዛኛው የሀገሪቱ አከባቢ እየጣለ ያለው ዝናብ በተወሰኑ አከባቢዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የብሄራዊ ሜትሮለጂ ኤጀንሲ ገለፀ።

ተጠናክሮ ሚቀጥለው ዝናብ በተወሰኑ አከባቢዎች ላይ ጎርፍ የሚያስከትል ቢሆንም፤ ለግብርናው ዘርፍ ግን ጠቃሚ ነው ብሏል ኤጀንሲው።

በኤጀንሲው የሜትሮሎጂ የአየር ሁኔታ እና የአየር ፀባይ ትንበያ ባለሞያ አቶ ታምሩ ከበደ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት፥ ደቡብ ምእራብ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ ህዝቦች፣ አብዛኛው ኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ክልሎች ጠንከር ያለው ዝናብ ተጠናክሮ የሚቀጠልባቸው አከባቢዎች ይሆናል።

በግብርና ሚንስቴር የግብርና ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ግርማሜ ጋሩማም፥ ከወቅቱ ቀድሞ በመላ ሀገሪቱ እየጣለ ያለው ዝናብ ለበልግ ምርታማነት እና ለቀጣይ ለመኸር እርሻውን ዝግጅት ከፍተኛ ጥቅም አለው ብለዋል።

የሚጥለው ዝናብ ከመጠን በላይ በመሆኑ አርሶ አደሮቹ ጎርፍ ወደ ማሳቸው እንዳይገባ ግን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸውም አቶ ግርማሜ አሳስበዋል።

የብሄራዊ አደጋ ስጋት እና ስራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ፥ ከበድ ያለውን ዝናብ ስጋቶች ተለይተው ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲደረግ ለሚመለከታቸው መረጃ መድረሱን ገልጿል።

በኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ዳይሬክተር ወይዘሮ አልማዝ ደምሴ፥ ከክልሎች አቅም በላይ የሚደረስ አደጋ ካለም ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን  ተናግረዋል።

በትዕግስት አብርሃም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.