Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ብስክሌት ሻምፒዮና ውድድር በመቀሌ ከተማ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች የሚሳተፉበት የ2015 የኢትዮጵያ ብስክሌት ሻምፒዮና ውድድር ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተጀምሯል።

ውድድሩን የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ወንድሙ ሃይሌና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የማህበራዊ ልማት ሽግግር ሃላፊ ክንደያ ገብረሕይወት (ፕ/ር) አስጀምረዋል።

አቶ ወንድሙ ሃይሌ ከሰኔ14 እስከ 18 ቀን 2015 ዓ.ም የሚካሄደው ውድድር የህዝብ ለህዝብ መልካም ግንኙነትን የበለጠ ያጠናክራል ብለዋል።

ውድድሩ በቀጣይ ዓመት ኢትዮጵያን ወክለው በዓለም አቀፍ የብስክሌት ውድድር የሚሳተፉ ብስክሌተኞችን ለመምረጥ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል ።

ክንደያ ገብረሕይወት (ፕ/ር) በበኩላቸው÷ በመቀሌ የተጀመረው የብስክሌት ውድድር በሁሉም የክልል አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ አስተዋጾ እንዳለው ገልጸዋል።

“ለዚህም ስፖርተኞች የሰላም አምበሳደር ልትሆኑ ይገባል” ነው ያሉት።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ ገብረስላሴ÷የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን የ2015 የብስክሌት ሻምፒዮና ውድድር በመቀሌ እንዲካሄድ በመፍቀዱ አመስግነዋል፡፡

ውድድሩ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.