9ኛው የአፍሪካ የሕዝብ አገልግሎት ቀን እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ሰኔ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዘጠነኛው የአፍሪካ የሕዝብ አገልግሎት ቀን ዛሬ በዚምባቡዌ መከበር ጀምሯል።
ቀኑ “ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስኬታማነት ብቁ የሆነ አህጉራዊ የሕዝብ አስተዳደር ያስፈልጋል” በሚል መሪ ሐሳብ ነው እየተከበረ የሚገኘው።
ለሦስት ቀናት የሚቆየው አከባበር የተዘጋጀው ÷ በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላም እና ደኅነነት የስራ ክፍል እና በዚምባቡዌ መንግስት ትብብር ነው፡፡
በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስኬት ውስጥ የፐብሊክ ሰርቪስ እና የአስተዳደር ማዕከላዊነት እንደማይታይ ተጠቅሷል፡፡
እንደ አዲስ የአፍሪካ ውህደት አጀንዳ፣ ለአህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በአገር አቀፍ ደረጃ በፐብሊክ ሰርቫንቱ ብቃት እና ክህሎት ላይ በመተማመን በአፍሪካ መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ለማሳደግ መሰራት እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡
በዚህም በአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ልማት ለማፋጠን ያለውን የላቀ ዓላማ ለማሳካት ያስችላል መባሉን የአፍሪካ ሕብረት መረጃ ያመላክታል።
የአፍሪካ የሕዝብ አገልግሎት ቀን ሐሳብ የተጠነሰሰው በፈረንጆቹ 1994 በሞሮኮ ታንጂየር ከተማ የሕዝብ አገልግሎት ሚኒስትሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ፓን አፍሪካዊ ስብስባ ላይ መሆኑ ይታወሳል፡፡
በዚሁ ወቅት የአፍሪካ የሕዝብ አገልግሎት ቀን በየዓመቱ በፈረንጆቹ ሰኔ 23 እንዲከበር መወሰኑ ይታወቃል፡፡
ዓላማውም ለማሕበረሰብ አገልግሎቶች ክብር እና እውቅና መስጠት ነው፡፡