Fana: At a Speed of Life!

በሱዳን የሚገኙ ዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ እየተሠራ ነው – አምባሳደር ብርቱካን

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት በሱዳን የሚገኙ ዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ፡፡
በሱዳን ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያሉ ኢትዮጵያውያንን በሰላም ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማገዝ የተቋቋመው ብሄራዊ ግብረ ኃይል ካለፉት ሁለት ወራት በፊት ያከናወናቸውን ተግባራት ዛሬ ገምግሟል።
በግምገማውም እስካሁን በተገኘው ውጤት እና ባጋጠሙ ተግዳሮቶች ላይ ምክክር መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
በካርቱም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም ግብረ ኃይሉን ወክሎ የተከናወኑ ተግባራትን ሪፖርት አቅርቧል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ እና የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በግምገማው ላይ ባደረጉት ንግግር÷ “በሱዳን የሚገኙ ዜጎቻችንን ደኅንነት ለመጠበቅ መንግስት የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ነው” ብለዋል፡፡

መንግስት ዜጎችን ከሱዳን ለማስወጣት ካሳየው ቁርጠኛ አቋምና እየወሰደ ካለው ጠንካራ እርምጃ አኳያ በተከናወኑ ስራዎች የተገኙ መልካም ውጤቶችንና ያጋጠሙ ፈተናዎችን በግምገማው ላይ ማንሳታቸውን አምባሳደር ብርቱካን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡

በዚህም በቀጣይ ለምናካሂደው ስምሪት ጠቃሚ ሐሳቦችን ተለዋውጠናል ብለዋል አምባሳደሯ፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.