ኢጋድ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዝ ስትራቴጂ አጸደቀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና በድህረ ምርት ስብሰባ የሚደርሰውን ብክነት ለመከላከል የሚያግዝ ስትራቴጂ አጸደቀ።
የኢጋድ አባል ሀገራት የሚኒስትሮች ስብሰባ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና በድህረ ምርት ስብሰባ የሚደርሰውን የምርት ብክነት ለመከላከል ያግዛል ያለውን አዲስ ስትራቴጂ አጽድቋል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የስትራቴጂው መጽደቅ ቀጣናውን ወደፊት የሚያራምድ ቁልፍ ውሳኔ መሆኑን ገልጸዋል።
ስትራቴጂው በአባል ሀገራቱ ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች ለምግብ ብክነት መንስዔ የሆኑ ችግሮችን በመለየት መፍትሄ ለማበጀትና ለመተግበር አቅም ይፈጥል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የምግብ ደኅንነትን ለማረጋገጥ አቅም ይፈጥራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ደኅንነቱ ያልተጠበቀ ምግብ ሸማቹን በከፍተኛ ሁኔታ ከመጉዳቱ ባሻገር ቀጣናው በአፍሪካና በዓለም አቀፍ የምግብ ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆን መሰናክል መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የኢጋድ ቀጣና አሁን ላይ በምግብ ዋስትና መጓደል ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ መግባቱን ጠቅሰው÷ የምግብ ዋስትና ስትራቴጂው ከመቼውም ጊዜ በላይ ወሳኝና አስፈላጊ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
ስትራቴጂው ከኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና እና ጥራት ስትራቴጂና በፈረንጆቹ በ2018 ከጸደቀው የሀገሪቱ የምግብና የስርዓተ ምግብ ፖሊሲ ጋር ተጣጥሞ እንደሚተገበር ተናግረዋል፡፡
የሀገሪቱ የምግብና የስርዓተ ምግብ ስትራቴጂ በፈረንጆቹ በ2021 እንደጸደቀና ከቀዳሚ ግቦቹ መካከል የምግብ ደህንነትንና ጥራትን ማረጋገጥ አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ ከ2023 አስከ 2030 ባለው ጊዜ የምግብና የስርዓተ ምግብ ደህንነት ችግሮችን ለመፍታት የሚረዳ የምግብ ደህንነትና ጥራት ማረጋገጫ ስትራቴጂ በማዘጋጀት ወደ ስራ መግባቷን አስታውሰዋል፡፡
የሶማሊያ የግብርና እና መስኖ ሚኒስትር አሳድ አብድራዛቅ መሃመድ በበኩላቸው÷ የኢጋድ ቀጣናዊ የምግብ ዋስትና ስትራቴጂና የኢጋድ ድህረ ምርት ብክነት መከላከያ ስትራቴጂ ትግበራን እውን በማድረግ የምግብ ዋስትና ችግሩን ለመፍታት የአባል ሀገራቱ ትብብር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ችግሩ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ሁሉም የኢጋድ አባል ሀገራት ብሄራዊ የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ ስትራቴጂ ሊኖራቸው እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡