ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአዲስ የዓለም አቀፍ ፋይናንስ ስምምነት ጉባዔ ላይ እየተሳተፉ ነው
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 15 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፈረንሳይ ፓሪስ በአዲስ የዓለም አቀፍ ፋይናንስ ስምምነት ጉባዔ ላይ እየተሳተፉ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከልዑካን ቡድናቸው ጋር በጉባዔው ላይ ለመሳተፍ ፈረንሳይ መግባታቸው ይታወሳል።
በጉባዔው ላይ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የሳዑዲ ዓረቢያ ልዑል አልጋወራሽ መሃመድ ቢን ሰልማንን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ተገኝተዋል።
ጉባኤው በአየር ንብረት ለውጥ እና በዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች ዙሪያ በሀገራት መካከል አዲስ ስምምነት እንዲደረስ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
ተጋላጭ ሀገራት አሁን እየተጋፈጡት እና በቀጣይ ሊገጥማቸው ያለውን ችግር ለመቅረፍ የፋይናንስ ድጋፍ ሊመቻችላቸው ይገባል የሚል ሀሳብ በስፋት የሚንጸባረቅበትም ነው ተብሏል።
የባለብዙ ወገን የልማት ባንኮች ማሻሻያ፣ የብድር ጉዳይ፣ የፋይናንስ አቅርቦት እና የዓለም አቀፍ ታክስ ጉዳይ ጉባኤው በስፋት የሚመከርበት እንደሆነም ታውቋል።
ሀገራት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ሳቢያ የፊስካል እና የበጀት ችግር ስለገጠማቸው ለዜጎቻቸው መሰረታዊ አገልግሎት ለማድረስ መቸገራቸው ተገልጿል።
ጉባዔው በጤና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ እና ድህነትን በመዋጋት ላይ መፍትሔ ይዞ ይመጣል ተብሏል።
በተለይ የእዳ ጫና ላለባቸው ሀገራት የአጭር ጊዜ መፍትሔ መስጠት፣ የግል ዘርፉን መደገፍ ፣ የአየር ንብረት ተጽዕኖ የሚቋቋም ስርዓት መገንባት እና ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ ሀገራት ፋይናንስ ማመቻቸት ከጉባኤው የሚጠበቅ ግብ እንደሆነም ተገልጿል።
በዓላዛር ታደለ