በሽብር ወንጀል ተከሳሾች ላይ የቀረበውን የክስ ዝርዝር ዐቃቤ ሕግ ስምና ፊርማ አካትቶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሽብር ወንጀል በተከሰሱ ተከሳሾች ላይ የቀረበውን የክስ ዝርዝር ዐቃቤ ሕግ ፊርማ እና ስም አካትቶ አሟልቶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
ትዕዛዙን የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረሽብርና ሕገመንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ባሳለፍነው ሳምንት በነበረ ቀጠሮ የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ 27 በሌሉበት፣ 24 ተከሳሾች ደግሞ ባሉበት ባአጠቃላይ በ 51 ተከሳሾሽ ላይ የሽብር የወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።
በዕለቱ ለ13 ተከሳሾች ዝርዝር ክሱ በፍላሽ ከተዘጋጀ አንድ ማስረጃ ጋር እንዲደርሳቸው ተደርጎል።
በዚህ ጊዜ በተከሳሽ ጠበቆች በኩል ለ13 ተከሳሾች በደረሰው በክሱ ዝርዝር ላይ የኃላፊ ፊርማ ከነስሙ ተካቶ መቅረብ ነበረበት የሚሉ የመቃወሚያ መከራከሪያ ነጥቦች አንስተው ነበር።
በችሎቱ የተሰየሙት ዐቃቤ ሕግ በበኩላቸው÷ ከሳሽ ፍትሕ ሚኒስቴር ተቋም መሆኑን በመጥቀስ በክሱ ራስጌ ላይ የተቋማቸው ማህተም መኖሩን እና በተጨማሪነት የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት መጠቀሱን ገልጸው መልስ ሰጥተዋል።
በዚህ የክርክር ነጥብ ላይ ፍርድ ቤቱ መርምሮ በዛሬው ቀጠሮ በክሱ ላይ የኃላፊ ፊርማ ከነስሙ ተካትቶ ተሟልቶ የፊታችን ሰኞ ሰኔ 19 ቀን ከሰዓት በኃላ ክሱ እንዲቀርብ አዝዟል።
በተጨማሪም÷ቀደም ብሎ የክስ ዝርዝሩን የወሰዱ ተከሳሾች ክሱን እንዲመልሱና ስምና ፊርማ ተካትቶበት በድጋሚ ተረጋግጦ እንዲደርሳቸው ከችሎቱ ዳኛ ጥያቄ ቀርቧል።
በተከሳሽ ጠበቆች በኩል ግን ቀደም ብሎ ለ13 ተከሳሾች የደረሰው ክስ ባለበት ሆኖ ለቀሪ ተከሳሾች የሚደርሰው ክስ ብቻ ተሟልቶ ከቀረበ በቂ ነው የሚል መልስ ተሰጥቷል፤ፍርድ ቤቱም የጠበቆቹን ምላሽ ተቀብሏል።
በሌላ በኩል ÷በባለፈው ቀጠሮ በፍላሽ የተካተተ አንድ ማስረጃን ተከሳሾቹ ባሉበት ማቆያ ቤት በኮምፒዩተር ከጠበቆቻቸው ጋር እንዲመለከቱ ፍርድ ቤቱ የሰጠው ትዕዛዝን በሚመለከት ፖሊስ ሰፊ ጊዜ ከጠበቆቻቸው ጋር እንዲገናኙ በማድረግ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ጠቅሶ፤ ለ13 ተከሳሾች በፍላሽ የተሰጣቸውን ማስረጃ በሚመለከት ግን ፍላሽ በማስገባት በኮምፒዩተር እንዲመለከቱ ማድረግ አሰራሩ እንደማይፈቅድለት በመግለጽ በጽሑፍ መልስ አቅርቧል።
ይህን መልስ ተከትሎ የተከሳሾች ጠበቆች በፖሊስ የተሰጠው ምላሽ የተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ማስረጃ የመመልከት ሕገመንግስታዊ መብታቸውን የሚጥስ መልስ ነው በማለት ተቃውመው ተከራክረዋል።
ጠበቆቹ አክለውም÷ ተከሳሾቹ የታሰሩትም ሆነ በጥበቃ ስር የሆኑት በመንግስት መሆኑን በመጥቀስ በፍላሽ የቀረበባቸውን ማስረጃ የማየት መብታቸው በማንም መጣስ የለበትም የሚል መከራከሪያ ነጥብ አንስተዋል።
በከሳሽ ዐቃቤ ሕግ በኩል ደግሞ ተከሳሾቹ የሚገኙበት ጊዜያዊ ማቆያ ቦታ የቀረበባቸውን ማስረጃ ለማየት ምቹ አለመሆኑን ገልጾ ፖሊስ ሊገደድ አይገባም የሚል አስተያየት ሰጥቷል።
በተጨማሪም÷ ዐቃቤ ሕግ ክሱ ተሟልቶ ለሁሉም ከተዳረሰ እና ከተሰማ በኋላ ተከሳሾች የሚቆዩበት ቦታ ቆይተው በፍላሽ የቀረበባቸውን ማስረጃ ሊሰሙ ይችላሉ የሚል አስተያየትም አክሏል።
በፍርድ ቤቱ በኩል ግን ተከሳሾች የተፋጠነ ፍትሕ እንዲያገኙ በፍላሽ የቀረበውን ማስረጃ ኮምፒዩተር አዘጋጅቶ የሚመለከቱበት ቦታ የማመቻቸት ተቋማዊ መዋቅር መዘርጋት የፖሊስ ሃላፊነት መሆኑን ፍርድ ቤቱ ገልጿል።
በቀጣይ ቀጠሮ ክሱ ተሟልቶ ለተከሳሾች ከደረሰ በኋላ ትዕዛዙን ፖሊስ እንዲተገብር እንደሚደረግ ችሎቱ አስታውቋል።
በሌላ በኩል ዮርዳኖስ አለሜ የተባለ 18 ኛ ተከሳሽ ውክልና መስጠት እንዲችል ፍርድ ቤቱ የሰጠው ትዕዛዝ እንዳልተተገበረለት ገልጾ በድጋሚ ዛሬ አመልክቷል።
ፍርድ ቤቱም በፖሊስ ትዕዛዙ ያልተተገበረበት ሁኔታ ተገልጾ በድጋሚ በአጃቢ ውክልና እንዲሰጥ እንዲደረግ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ሌሎች ማለትም 11ኛ እና 50ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች በተመሳሳይ በአቅራቢያቸው ባለ ውልና ማስረጃ በመሄድ ውክልና መስጠት እንዲችሉ እንዲደረግ ታዟል።
በሌላ በኩል÷ በሰውነቱ ውስጥ ጥይት እንዳለበት በጠበቃው የተጠቀሰው ማስረሻ እንየው የተባለ 47ኛ ተከሳሽን በሚመለከት በግሉ በመረጠው የህክምና ተቋም አፋጣኝ በቂ ህክምና ማግኘት እንዲችል በቀረበ አቤቱታ መነሻ ፍርድ ቤቱ በግል የህክምና ተቋም በአጃቢ ሄዶ ህክምና እንዲያገኝ እንዲደረግ ታዝዟል።
በሌላ በኩል ÷በባለፈው ቀጠሮ ፎቷችን ተለጥፎ ንፁህ ሆኖ የመገመት መብታችን ተጥሶ ተፈርጀን በመንግስት መገናኛ ብዙሃን የተላለፈብን ዘገባ የቤተሰቦቻችንን እና የእኛን ስነልቦና የሚጎዳ በመሆኑ ከአርካይቭ ላይ ይውረድልን በማለት ተከሳሽ ሲሳይ አውግቸው (ረ/ፕ) እና ዳዊት በጋሻው ያቀረቡትን አቤቱታ ፍርድ ቤቱ መርምሮ ትዕዛዝ ሰጥቶበታል።
በዚህም ትዕዛዝ የተከሳሾቹ በፍርድ ቤት ሂደት ላይ እያሉ ንፁህ ሆኖ የመገመት መብታቸውን በሚጥስ መልኩ ሽብርተኛ በሚል ዘገባ ያቀረቡ የመንግስት የመገናኛ ብዙሃኖች ካሉ ዘገባውን ከአርካይቭም ሆነ ከማህበራዊ ሚዲያ እንዲያወርዱ እና መልስም እንዲሰጡበት በሁለት ዳኞች አብላጫ ድምጽ በአንድ ዳኛ የልዩነት ሀሳብ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
ባሳለፍነው ሳምንት ዐቃቤ ሕግ የሽብር ወንጀል ክስ ከተመሰረተባቸው 51 ተከሳሾች መካከል ወንደሰን አሰፋ (ዶ/ር) ፣መስከረም አበራ፣ መሰረት ቀለመወርቅ (ዶ/ር) ፣ ሲሳይ አውግቸው( ረ/ፕ) ፣ዳዊት በጋሻሁ፣ ገነት አስማማው፣ ጎበዜ ሲሳይ ፣መንበረ አለሙ፣ ተስፋዬ መኩሪያ፣ይገኙበታል።
በታሪክ አዱኛ