Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ቤልጂየም በትብብር መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የቤልጅየም አምባሳደር ስቴፋን ቲጀን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ ሀገራቱ በተለያዩ ዘርፎች በትብብር እና በቅንጅት  መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ቤልጂየም በተለያዩ ዘርፎች በትብብር በመስራት የጠበቀ ግንኙነት የመሰረቱ  ሀገራት መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በተለይም በግብርናው ዘርፍ በአበባና ቡና ምርት ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን÷ኢትዮጵያ ለግብርና ያላትን ምቹ ስነ-ምህዳር፣ ሰፊ መሬት በመጠቀም ዘርፉን ለማዘመን እየሰራች መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ለግብርናው ዘርፍ ያሉትን ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም እንዲሁም የሕዝብ ንቅናቄ በመፍጠር ግብርናውን ለማዘመን እየተሰራ  መሆኑን ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በስንዴ፣ በአረንጓዴ አሻራ እና በሌማት ትሩፋት እየተተገበሩ ያሉ  ስራዎች ግብርናውን ለማዘመን እና ሽግግሩን ለማፋጠን ትልቅ ድርሻ አላቸው ማለታቸውንም  የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የግብርናው ልማት በታሰበው ፍጥነት እንዲሄድ ከቤልጂየም ጋር በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ የቴክኒክ ድጋፎችና ተያያዥ ግንኙነቶች እንዲጠናከሩ ሁለቱም በጋራ እንደሚሰሩ ተጠቅሷል፡፡

በሀገራቱ ያሉትን ምቹ ሁኔታዎች ታሳቢ ያደረጉ ድጋፎች እና ትብብሮች እንደሚደረጉም በውይይቱ ወቅት ተነስቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.