ኃይለማርያም ደሳለኝ ከሴራሊዮን ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ኅብረትን ተልዕኮ አንግበው የሴራሊዮንን ምርጫ ታዛቢዎች የሚመሩት ኃይለማርያም ደሳለኝ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ማዳ ዎኒ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት የአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካዊ ጉዳዮች እንዲሁም የሠላምና ደኅንነት ኮሚሽነር የሆኑት አምባሳደር ባንኮሌ አዲኦዬ እና የኅብረቱ የግጭት መከላከል እና አሥተዳደር ዳይሬክተር ፓቲየንስ ቺራድዛ ተገኝተዋል፡፡
የቀድሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ÷ የአፍሪካ ኅብረት በሰጣቸው ተልዕኮ መሠረት የሚመሩት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን ሠላማዊ እና ተዓማኒ ሀገራዊ ምርጫ በሴራሊዮን እንዲካሄድ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
ኃይለማርያም ደሳለኝ ÷ ከሀገራዊ ምርጫው ጋር በተገናኘ ከሚመለከታቸው ሲቪል ማኅበራት ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተቆጣጣሪ ኮሚሽን እንዲሁም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተገናኝተው በምርጫው ላይ ስላላቸው ሚና እና ተሳትፎ መረጃዎችን ተለዋውጠዋል፡፡
ከሀገሪቷ ብሔራዊ የዴሞክራሲ ኮሚሽን ፣ ብሔራዊ የደኅንነት ቢሮ እንዲሁም የኅግ ጉዳይ ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች በሴራሊዮን ወቅታዊ የፖለቲካ እና የጸጥታ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ እንደተሰጣቸውም ነው የአፍሪካ ኅብረት በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ ያመላከተው፡፡
በሀገሪቱ ለሚካሄደው ምርጫ ሴራሊዮን ያላትን ዝግጁነትም አረጋግጠውላቸዋል፡፡