የኢትዮጵያ ፓስፖርት ለሌላ አገር ዜጎች በህገ ወጥ መንገድ እየተሰጠ ይገኛል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፓስፖርት ለሌላ አገር ዜጎች በህገ ወጥ መንገድ እየተሰጠ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡
ከሽብርተኝነት እስከ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች ማስፈጸሚያ ሊውል የሚችለውን ድርጊት ማስቆም ያልተቻለበትን ምክንያት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ ተቋማትን ጠይቋል።
የኢሚግሬሽን ዜግነት አገልግሎት እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ችግሩ መኖሩን እንደሚያምኑ ገልፀዋል።
በኢሜግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የጉዞ ሰነዶች አሰጣጥ ዳይሬክተር ቡድን መሪ ዓለምጸሀይ አንባቸው÷ ከአገር የሚወጡ የኢትዮጵያን ፓስፖርት በህገ ወጥ መንገድ የሚይዙ የውጭ ዜጎች በርካቶች ስለመሆናቸውም ተናግረዋል።
ይህ ደግሞ ለአገር ትልቅ አደጋ እንዳለው ነው የሚጠቅሱት።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የባህል፣ ቋንቋ እና ማንነት መጋራት ያላት በመሆኑ ለማጥራት ሂደቱ ትልቅ ፈተና እንደሆነበት አንሰተዋል።
ከዚህ በላይ በተቋማት ውስጥ ያለው ብልሹ አሰራር ለችግሩ እድል ሰጪ ሆኖ መገኘቱንም ነው ያብራሩት።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጄንሲ ዋና ዳሬክተር ዮናስ አለማሁ በበኩላቸው የሀሰተኛ መረጃ ፈተና እና የፈፃሚዎች ክፍተት ችግሩን እንዳባባሰው ይናገራሉ።
የሲቪል ምዝገባ የነዋሪዎች አገልግሎት እና የኢሜግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ጉዳዩን የፈጸሙ አካላት ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልፀዋል፡፡
በዚህም የኢሜግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አንድ መቶ ሃያ አምስት ግለሰቦች በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረጉን አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ደግሞ አንድ መቶ ሀምሳ ሶስት ግለሰቦችን በህግ ተጠያቂ ማድረጉን ጠቁሟል።
ከዚህ ወስጥም ሀምሳ ዘጠኘ የሚሆኑት የተቋሙ ሰራተኞች መሆናቸውን ገልጿል፡፡
በሲሳይ ጌትነት