Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መሪዎች ጋር መክረዋል -የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፈረንሳይ ፓሪስ በተካሄደው ከአዲስ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስምምነት ጉባዔ ጎን ለጎን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መሪዎች ጋር በሁለትዮሽና አህጉራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአዲስ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስምምነት ጉባዔ በኢትዮጵያም አልፎ የአፍሪካ ከዛም ባሻገር በሌሎች አህጉራት የሚገኙ ታዳጊ ሀገራት እያጋጠማቸው የሚገኙትን የፋይናንስ በተለይ የዕዳ አከፋፈል ስርዓት እንዲሁም እያደረሰ ያለውን ጫና በተመለከተ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትም የአሰራር ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚገባቸው እና ተቋማቱ ቃል የገቡትን ወደ ተግባር መቀየር እንደሚገባቸው መናገራቸውንም ሚኒስትር ዴዔታዋ ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም ፥ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በዓለም አቀፍ ደረጃ ቃል የተገቡ ድጋፎች በአፋጣኝ መፈፀም እንደሚገባቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኩል የተያዙ ቀጣይነት ያላቸው የልማት ግቦች በተመለከተም ለታዳጊ ሀገራት ቃል የተገቡ በርካታ ድጋፎች መኖራቸውን ጠቁመው ፤ እነዚህንም ወደ ተግባር ማስገባት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በዓለም አቀፍ መድረኩ የልማት ካፒታልን ለታዳጊ ሀገራት በሚገባው ልክ ማቅረብ እንደሚገባ በአፅንዖት ተናግረዋል ነው ያሉት፡፡

ለታዳጊ ሀገራት አስፈላጊ የሆኑ የልማት ፋይናንስን በተመለከተ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ተቋማት የአረንጓዴ ልማትን መደገፍ እንደሚገባቸው ተናግረው ፤ ትኩረት እንዲሰጡትም አሳስበዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፡፡

ዓለም በዓየር ንብረት ለውጥ ውስብስብ ፈተና ውስጥ ባለችበት ወቅት እንደ ኢትዮጵያ ተጨባጭ መፍትሄ እያቀረቡ ያሉ ሀገራት ተገቢውን ድጋፍ ሊያገኙ ይገባልም ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምግብ ራስ ለመቻል ኢትዮጵያ እያደረገች ያለችውን ውጤታማ ተሞክሮ በመድረኩ ማቅረባቸውንም ገልፀዋል፡፡

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ ከውጭ የሚመጣውን ተፅዕኖ ለመቋቋም ያን የሚመጥን ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትር ዴዔታዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአዲስ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስምምነት ጉባኤ ጎን ለጎን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መሪዎች ጋር የሁለትዮሽና አህጉራዊ ጉዳዮችን በማንሳት መወያየታቸውንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከፈረንሳይ፣ ከኬንያ እና ከሳውዲ አረቢያ ሀገራት መሪዎች እንዲሁም ከተመድ ዋና ፀሃፊ፣ ከዓለም ባንክ እና ከዓለም የፋይናንስ ተቋም ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል ነው ያሉት ፡፡

በሌላ በኩል የበልግ እርሻ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ በሲዳማ፣ በደቡብና፣ በደቡብ ምዕራብ ክልሎች በአጠቃላይ ወደ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም እስከ ሰኔ 11 2015 ዓ/ም ባለው መረጃ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት በላይ ታርሷል ፤ ከዚህም ውስጥ 2 ነጥብ6 ሚሊየን በዘር ተሸፍኗል ብለዋል፡፡

በመኸር አብቃይ አካባቢዎች ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ ክልሎች አፈር ማዳበሪያ እጥረት እንዳለ ቅሬታ እየተነሳ መሆኑን ገልፀው ፥ ይህን ለመቅረፍ መንግስት በትኩረት እየሰራ እና መፍትሔ ያላቸውን እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.