Fana: At a Speed of Life!

ራዕይ ያለው አመራር ሲኖር የሚሰራው ስራ በተግባር ይታያል – ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ራዕይ ያለው አመራር ሲኖር የሚሰራው ስራ በተግባር ይታያል ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ÷ በሲዳማ ክልል ሐዋሳ ዙሪያ ወረዳ በሞዴል ቤተሰብ የዶሮ እርባታ መንደርን መርቀዋል፡፡

በሚሰሩ ስራዎች ላይ ፍላጎት ከታከለበት መለወጥና ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም ገልፀዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷በግብርናው ዘርፍ በኩታ ገጠም እንደሚሰራ ሁሉ በእንስሳቱም ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።

እየተሰራ ባለው የሌማት ቱርፍት ስራ የሲዳማ ክልል በቀዳሚነት ደረጃ እያከናወነው እንዳለም ጠቅሰዋል፡፡

ከ26 ሺህ በላይ የዶሮ፣ የወተት፣ የንብ እና የአሳ ማራቢያ ቦታዎች እንዳሉም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ደስታ ሌዳሞ÷ በግብርናው ብቻ የተሳለጠ ለውጥ ማምጣት ስለማይቻል በእንስሳትና በዶሮ ልማት እርባታ ላይ ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

የዶሮ እና የእንቁላል ምርጥ ዘር ለአከባቢው ማህበረሰብ የሌማት ቱሩፋቱን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር አሁን የተመረቀው ሞዴል የዶሮ እርባታ መንደር ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

በሞዴል የዶሮ እርባታው ላይ የተሰማሩ ወጣቶች በተለያዬ የትምህርት ዘርፍ የተመረቁ መሆናቸውም ተገልጿል።

በጥላሁን ይልማና በጀማል ከዲሮ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.