Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ በፓሪሱ ጉባዔ ለአፍሪካውያን የልማት ፋይናንስ ድጋፍ እንዲጨምር በአፅንኦት ጠይቀዋል – ቢልለኔ ስዩም

አዲስ አበባ ሰኔ 17፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፓሪሱ አዲስ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስምምነት ጉባዔ ላይ ለአፍሪካውያን የሚደረገው የልማት ፋይናንስ ድጋፍ እንዲጨምር በአፅንኦት መጠየቃቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከልዑካን ቡድናቸው ጋር ለሁለት ቀናት በፈረንሳይ ፓሪስ በተካሄደው አዲስ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስምምነት ጉባዔ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ፥ ኢትዮጵያ በጉባኤው ስለነበራት ተሳትፎና ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶችን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጉባዔው ፥ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አማካይነት በዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ላይ አቋሟን ያንጸባረቀችበት እንዲሁም የአፍሪካውያንና የታዳጊ ሀገራትን ድምፅ ያሰማችበት ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር አፍሪካ ተደራራቢና ውስብስብ የሆኑ የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት፣ የዕዳ ጫና እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ላመጣቸው ቀውሶች ተጋላጭ መሆኗን ማንሳታቸውንም ተናግረዋል።

የአፍሪካ ሀገራት ፍትሐዊ እና ዘላቂ ዕድገት እንዲኖራቸው የፋይናንስ አቅርቦቱ መሻሻል እና መጠናከር እንዳለበት የኢትዮጵያን ግልፅ ጥያቄ ማቅረባቸውንም ነው ያብራሩት።

በተለይም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትን የበለጠ ተራማጅ ማድረግ እንደሚገባ መጠቆማቸውንና ከዚህ ቀደም ቃል የተገቡ ስምምነቶችን መተግበር እንዳለባቸው መናገራቸውንም እንዲሁ።

በተለይ ለአፍሪካ ሀገራት ሊሰጡ የታሰቡ የልማት ፋይናንስ ድጋፎች በተጨባጭ ፈሰስ እንዲደረጉና አቅርቦቱም እንዲጨምር በአፅንኦት ጠይቀዋል ነው ያሉት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊዋ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መሆኗን ለጉባኤው ማቅረባቸውን ያነሱት ቢልለኔ፤ ወደ አረንጓዴ ልማት ሽግግር ለሚያደርጉ አገራት የበለጠ የገንዘብ ድጋፍ መደረግ እንዳለበት መጠቆማቸውን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገለጻቸው ኢትዮጵያ በስንዴ ልማትና በአረንጓዴ አሻራ አመርቂ ውጤቶችን ማምጣቷንም ለጉባኤው አብራርተዋል ማላታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

ኢትዮጵያ በግብርናውና በሌሎችም መስኮች የጀመረቻቸው የልማት ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ በራስ አቅም ከሚደረገው ጥረት ባሻገር ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የፋይናንስ ድጋፋቸውን በማጠናከር የታሰበው ዕድገት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲሳካ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጉባዔው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች፣ ከአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የፋይናንስ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ ስለመወያየታቸውም ቢልለኔ ገልጸዋል።

በዚህም ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ኃላፊ፣ ከአዲሱ የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት፣ ከፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ ከአፍሪካውያን መሪዎች ጋር በተደረጉ ውይይቶች ኢትዮጵያን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስምምነቶች ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።

ይህም የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በውጤታማነት እያደገ ለመምጣቱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.