Fana: At a Speed of Life!

ጀነራል አበባው የልዩ ኃይል መልሶ የማደራጀት ቀሪ ሥራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ሰኔ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጀነራል አበባው የልዩ ኃይል መልሶ የማደራጀት ቀሪ ሥራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ አሳስበዋል፡፡

ሕዝባዊ ሚሊሻን መልሶ ለማደራጀት እና የልዩ ኃይል መልሶ የማደራጀት ሥራ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለመገምገም ያለመ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይት መድረኩ የሀገር መከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ የከተማ አስተዳደሮች ፖሊስ ኮሚሽነሮች እና የክልል የፀጥታ ቢሮ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የመከላከያ ሰራዊት ምክትል ኢታማጆር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት÷ የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ጠንካራ የፀጥታ መዋቅር ያስፈልጋል፡፡

በፀጥታ ተቋማት የተደራጀ ጥናት እና ውይይት በሀገራዊ ኃላፊነት ለሁሉም የሚጠቅም አንድ ወጥ የሆነ የሠራዊት ኃይል መፍጠር ተችሏል ነው ያሉት።

ልዩ ኃይልን መልሶ ለማደራጀት የተሰራው ሥራ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ በግምገማው መታየቱንም አስረድተዋል፡፡

እስካሁን የተከናወነው ተግባር በተቀመጠለት ዕቅድ መሠረት መከናወኑን ጠቁመው÷ ሥራው እንዲሳካ አስተዋጽዖ ላደረጉት አካላት ምስጋና ማቅረባቸውን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

በቀጣይም የቀረው የልዩ ሃይል መልሶ የማደራጀት ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ነው ጀነራል አበባው ያሳሰቡት።

ሕዝባዊ ሚሊሻን መልሶ በማደራጀት እና በማሰልጠን በየቀበሌው ከፖሊስ ጋር በማቀናጀት የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት እንዲጠብቅ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በአጽንዖት ተናግረዋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በበኩላቸው÷ ሕዝባዊ ሚሊሻውን ማደራጀት እና ማሰልጠን ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.