በአማራ ክልል በውል እርሻ ስምምነት ከግማሽ ሚሊየን በላይ ሄክታር መሬት እንደሚለማ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በውል እርሻ ስምምነት አተገባበር ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
የቢሮው ም/ሃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው÷መድረኩ በውል እርሻ የሚመረቱ ሰብሎች ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ፣ የግብይት ችግርን ለመፍታት እና የውል አስተዳደርን ለማሻሻል ያለመ መሆኑን አንስተዋል።
የውል እርሻ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶአደሩ ለማስተዋወቅ እድል እንደሚፈጥር እና የግብርና ግብዓት አቅርቦትና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያሰገኝ አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም አስመራቹ ለአርሶአደሮች የእውቀት ሽግግር እንዲያደርግ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባለፈ የግብይት ወጪን እና የገበያ ስጋትን እንደሚቀንስ አንስተዋል፡፡
ለውይይት መነሻ ሪፖርት ያቀረቡት የርዕሰ መስተዳድሩ ዴሊቨሪ ዩኒት አማካሪ አቶ ውብሸት ሙላት÷ የውል እርሻ አፈፃፀም፣ ያጋጠሙ ችግሮችና የመፍትሔ ሀሳቦችን አቅርበዋል።
በመድረኩ የውል እርሻ ስምምነት የሕግ ማዕቀፍም በዝርዝር ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት የቢሮው መረጃ ያመላክታል፡፡
በአማራ ክልል በ2015/16 የመኸር ምርት ዘመን በውል እርሻ ስምምነት በአኩሪ አተር፣ በሰሊጥ፣በማሾ፣በቦሎቄ እና በሌሎች ሰብሎች 523 ሺህ 493 ሄክታር መሬት እንደሚለማ ተጠቁሟል፡፡
በዚህም 7 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት የታቀደ ሲሆን÷ ከ300 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉም ተገልጿል፡፡