‘በታሪክ ትልቁ የሐጅ ጉዞ’ በሳዑዲ ዓረቢያ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተያዘው ዓመት የሐጂ ተጓዦች ቁጥር ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን እንደሚልቅ እና በታሪክ ትልቁ ሆኖ እንደሚመዘገብ ተነግሯል፡፡
በትናንትናው ዕለት በሳዑዲ ዓረቢያ መካ የተጀመረው የሐጅ ተጓዦች ዓመታዊ ሥነ-ሥርዓት በቁጥር ከፍተኛ ሑጃጆችን በማስተናገድ በታሪክ እንደሚመዘገብ የሳዑዲ የሐጅ እና ኡምራህ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ በየሀገራቱ የጉዞ ገደቦች ተጥለው እንደነበር ይታወሳል፡፡
በዚህ ሳቢያም በፈረንጆቹ 2020 በሳዑዲ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዲታደሙ የተፈቀደ የሐጅ ተጓዦች ቁጥር10 ሺህ ያህል ነበር፡፡
በፈረንጆቹ 2021 ደግሞ 59 ሺህ የሐጅ ተጓዦች ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ መካ እንዲገቡ ሲፈቀድላቸው÷ ባለፈው ዓመት 1 ሚሊየን ሑጃጆች በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ታድመዋል፡፡
ዕሁድ አመሻሽ ላይ የሐጅ ተጓዦች (ሑጃጆች) የፀሎት ሥርዓት ወደ ሚጀመርበት እና መካ ከሚገኘው ታላቁ መስጂድ 8 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ሚገኘው ሚና ጉዞ ጀምረዋል።
በመጨረሻም ነቢዩ ሙሐመድ የመጨረሻ ስብከታቸውን ወዳደረጉበት የአረፋ ተራራ ላይ እንደሚሰባሰቡ አልጀዚራ ዘግቧል።
በሥነ-ሥርዓቱ ወቅት የሚኖረው የአየር ፀባይ ሁኔታም እስከ 45 ዲግሪ ሴሊሺየስ እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡