ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ የሽብር ወንጀል ክስ ባቀረበባቸው በእነ ወንደሰን አሰፋ (ዶ/ር) መዝገብ የተካተቱ 6 ተከሳሾችን የክስ ዝርዝር በንባብ አሰማ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ የሽብር ወንጀል ክስ ባቀረበባቸው በእነ ወንደሰን አሰፋ (ዶ/ር) መዝገብ የተካተቱ ስድስት ተከሳሾችን የክስ ዝርዝር በንባብ አሰምቷል።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ-ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ከዚህ በፊት በነበረ ቀጠሮ በ11 ተከሳሾች የክስ ዝርዝር ላይ ዐቃቤ ሕግ ስምና ፊርማ አሟልቶ እንዲቀርብ የተሰጠውን ትዕዛዝ ለመጠባበቅ በያዘው ቀጠሮ መሰረት ተሰይሟል።
በዚህም መሰረት ከፍርድ ቤቱ ሬጅስትራል ተወካይ ቀርበው የቀሪ 11 ተከሳሾች የክስ ዝርዝር መሟላቱን በማረጋገጥ የክስ ዝርዝሩ ከአንድ የፍላሽ ማስረጃ ጋር እንዲደርሳቸው ተደርጓል።
ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን ማንነት በችሎት በማረጋገጥ እንዲመዘገቡ አድርጓል።
በዚህ ጊዜ በክሱ ተራ ቁጥር በ7ኛ ተከሳሽነት የተጠቀሱት አለልኝ ምህረቱ የተባሉ ግለሰብ ከዚህ በፊት በተጠረጠሩበት ሁከትና አመጽ ማስነሳት ወንጀል ተጠርጥረው በዋስ መውጣታቸውን በመጥቀስ ባሳለፍነው ቅዳሜ ዕለት የፍርድ ቤት መጥሪያ በሌለበት፣ ከሕግ ውጪ ”በፖሊስ ተይዤ መቅረቤ” አግባብ አይደለም ሲሉ ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ በከሳሽ ዐቃቤ ሕግ እና በተከሳሽ በኩል ክርክር ተደርጎል።
በዚህ አቤቱታ ላይ ዐቃቤ ሕግ ተከሳሽ በመሆናቸው መሰረት መያዛቸው ተገቢ ነው በማለት አስተያየት ሰጥቷል።
ከዚህ በፊት በምን ጉዳይ ነው ተጠርጥረው የነበረው? ተብሎ በፍርድ ቤቱ የተጠየቀው ዐቃቤ ሕግ በጉዳዩ ዙሪያ መረጃ እንደሌለው በመግለጽ መልስ ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱም የ7ኛ ተከሳሽ አቤቱታንና የዐቃቤ ሕግ የመከራከሪያ ነጥብን መርምሮ ግለሰቡ በቀረበባቸው ክስ ላይ ከፍርድ ቤቱ እንዲቀርቡ መጥሪያ ባልደረሰበት ሁኔታ ላይ ያለመጥሪያ ተይዘው እንዲቀርቡ የተደረገበት ሂደት አግባብ አይደለም በማለት በቀጣይ በፍርድ ቤቱ የመጥሪያ ትዕዛዝ እንደሚሰጥበት በመግለጽ ግለሰቡ ከእስር እንዲፈቱ መፍቻ እንዲጻፍ ብይን ሰጥቷል።
በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ በቀጣይ ቀጠሮ የፌዴራል ፖሊስ ግለሰቡን ካለ ፍርድ ቤት መጥሪያ ባሳለፍነው ቅዳሜ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ያደረገበት ሂደትን ቀርቦ ያስረዳ በማለት ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በዚህ ጊዜ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ ላይ የተጠቀሱ 7ኛ ተከሳሽን ጨምሮ አጠቃላይ ያልቀረቡ ተከሳሾች በችሎት እንዲቀርቡ ፖሊስ መጥሪያ እንዲያደርስለት ጠይቋል።
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ÷ ክሱ ላልቀረቡ ተከሳሾች ተሟልቶ ለችሎቱ ባልደረሰበት ሁኔታ ላይ መጥሪያ ትዕዛዝ መስጠት ተገቢነት የሌለው ነው በማለት አልተቀበለውም።
ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ” እኛ አስተያየት ስንሰጥ ችሎቱ መርምሮ ብይን ሊሰጥበት ሲገባ በተናጠል የሚደረግ ምልልስ ተገቢነት ስለሌለው ወደፊት ሊታረም ይገባል በማለት ለችሎቱ ዳኞች የዕርምት አስተያየት ሰጥቷል።
በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ በባለፈው ቀጠሮ በተከሳሾች በኩል የቀረበው አቤቱታ ማለትም የተከሳሾች ጉዳይ በፍርድ ቤት በሂደት ላይ እያለ ንፁህ ሆኖ የመገመት መብታቸውን በሚጥስ መልኩ ዘጋቢ ፊልም የሰራ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ካለ ከአርካይቭና ከማህበራዊ ሚዲያ በማውረድ መልስ ይሰጥበት በማለት የሰጠውን ትዕዛዝ ተከትሎ ችሎቱ ከመንግስት መገናኛ ብዙሃን የቀረቡ ተወካዮች መኖራቸውን ለማረጋገጥ ጥሪ ያደረገ ቢሆንም የቀረበ ተወካይ ባለመኖሩ በቀጣይ ቀጠሮ ትዕዛዝ እንደሚሰጥበት ገልጿል።
በቀጣይም ችሎቱ ተከሳሾች ላይ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን የክስ ዝርዝር ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ተራ ቁጥር ለተጠቀሱ ተከሳሾች በንባብ አሰምቷል።
ይህ በተወሰኑ ተከሳሾች በንባብ የተሰማው የክስ ዝርዝር 72 ገጾች ያሉት ሲሆን÷ የተናጠልና የቡድን ተሳትፎ ተዘርዝሮ በክሱ ላይ በዐቃቤ ሕግ ሰፍሯል።
በንባብ በተሰማው ዝርዝር ክስ ላይ እንደተመላከተው ተከሳሾቹ ”መነሻችን አማራ መድረሻችን ኢትዮጵያ” በሚል የፖለቲካ እና የርዕዮት አላማ ለማራመድ በማሰብ፣ሀገሪቱን እያስተዳደረ ያለውን መንግስት በተለያየ ወታደራዊ ስልት እና ስትራቴጅ በመውጋት፣ የአማራን ሕዝብ ክብር እና ኩራት በወታደራዊ ኃይል መመለስ፣ የመንግስትን ኃይል በማያዳግም መልኩ መደምሰስ፣ የአማራ ህዝብ በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ፣ የክልሉን ገዥ ፓርቲ ማስወገድ ፣ የሀገሪቱን ማዕከላዊ ስልጣን መቆጣጠር ፣ የአማራ ክልል የሚዋሰኑባቸው መንገዶችን መዝጋት፣ ፣ሕዝብን ማሸበር እና መንግስትን አስገድዶ ከስልጣን ማውረድ የሚሉ የሽብር ተግባር ድርጊቶችን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ ዘርዝሯል።
በተለይም ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ ተፈፅሟል ባለው የሽብር ድርጊት እንቅስቃሴ የማህበራዊ አገልግሎት መቋረጡን ፣ አመጽ መነሳቱን ጠቅሶ፤ በዚህ የሽብር ተግባር ደግሞ አጠቃላይ 217 ሰዎች ህይወት ማለፉን፤ 297 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን አስረድቷል፡፡
ከዚህ ባለፈም 1 ቢሊየን 298 ሚሊየን 346 ሺህ 276 ብር በላይ በሚገመት ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል በማለት በክሱ ዝርዝር ላይ አስፍሯል።
በዚህ መልኩ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 32/1/ሀ/ለ/፣ 35 እና 38፤ እና የሽብር ወንጀልን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/ 2012 አንቀፅ 3 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፍ የሚል ክስ በተከሳሾቹ ማቅረቡ ተጠቅሶ በችሎቱ በንባብ ተሰምቷል።
ችሎቱ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር በተጠቀሱ ተከሳሾች ክስ በንባብ እየተሰማ በነበረበት ወቅት መብራት በመጥፋቱ ምክንያት ክሱን በንባብ የማሰማት ተግባሩን ለማቋረጥ ተገዷል።
ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹን በጨለማ ይዞ ለመዘዋወር ለፖሊስ አስቸጋሪ መሆኑን በመጥቀስ ቀሪውን ክስ ግን በተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰማ ችሎቱን ጠይቋል።
ችሎቱ የቀሪ ተከሳሾችን የክስ ዝርዝር በንባብ ለማሰማት ለፊታችን ዓርብ ለተዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በዐቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን የሽብር ወንጀል ክስ ዛሬ በችሎት ተገኝተው ከተከታተሉ ተከሳሾች መካከል ወንደሰን አሰፋ (ዶ/ር) ፣ መስከረም አበራ፣ መሰረት ቀለመወርቅ (ዶ/ር)፣ ሲሳይ አውግቸው (ረ/ፕ)፣ ዳዊት በጋሻሁ፣ ገነት አስማማው፣ ጎበዜ ሲሳይ ፣መንበረ አለሙ፣ ተስፋዬ መኩሪያ ፣ማስረሻ እንየው፣ ታደሰ ወንዳይነው፣ አንደበት ተሻገር፣ ዳዊት እባቡ፣ ጨምሮ 23 ግለሰቦች ይገኙበታል።
በአጠቃላይ የሽብር ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው 51 ግለሰቦች ላይ ሲሆን÷ 27 ቱ በሌሉበት የተከሰሱ ናቸው።
በታሪክ አዱኛ