Fana: At a Speed of Life!

“የወል እውነቶችን በማጽናትና ልዩነቶችን በንግግር በመፍታት ሰላማችንን ማስቀጠል ይገባል” – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) “የወል እውነቶችን በማጽናት፤ ልዩነቶችን በንግግር በመፍታት ሰላማችንን ማስቀጠልና ማጽናት አለብን” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።

በአዲስ አበባ ከተማ “መፍጠንና መፍጠር፤ የወል እውነቶችን የማፅናት ቀጣይ የትግል ምዕራፍ” በሚል እስከ ወረዳ በየደረጃው ለሚገኙ 4 ሺህ162 አመራሮች ባለፉት 4 ቀናት ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቅቋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ አመራሩ ለሀገረ መንግስት ግንባታ ተግዳሮት የሚሆኑ ጉዳዮችን በማረምና በማስተካከል ብሔራዊ መግባባትን ሊፈጥሩ የሚችሉ ስራዎችን በመስራት የወል እውነቶችን ማጽናት ይገባዋል ብለዋል፡፡

“ከውስጥ ያለንን አቅማችንን በሚገባ በመጠቀም መፍጠንና መፍጠር ይገባናል” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

“መበተንና መለያየት አቅማችንን ስለሚያሳንሱ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በመጠበቅ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ማድረግ  ይገባል” ነው ያሉት፡፡

የዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታ አጠቃላይ በሚሰሩ ስራዎች ውስጥ የራሱ ተጽዕኖ እንዳለው ጠቁመው÷በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ በመሆን በርካታ ሀገራዊ ለውጦችን ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል።

ሰላምና ጸጥታ ላይ ብዙ ጊዜ ችግር የሚገጥመው የወል እውነቶችን አጥብቆ ባለመያዛዝ በመሆኑ የወል እውነቶችን በማጽናትና ልዩነቶችን በንግግር በመፍታት ሰላምን ማስቀጠልና ማጽናት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮችም በቪዲዮ ኮንፈረንስ የማጠቃለያ ሀሳቦችን እና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን መስጠታቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.