Fana: At a Speed of Life!

ሕዝበ ሙስሊሙ የአረፋ በዓልን ሲያብር በአንድነት እና በመረዳዳት ሊሆን ይገባል – ሼኽ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕዝበ ሙስሊሙ የአረፋ በዓልን ሲያብር በአንድነት፣ በመረዳዳትና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን  እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ፕሬዚዳንት ሼኽ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ገለጹ፡፡

ሼኽ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ÷ለ1 ሺህ 444ኛ ዓመተ ሂጂራ የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በሳዑዲ ዓረቢያ የሃጂ ስነ ስርዓት ላይ የሚገኙት ፕሬዚዳንቱ ÷በዘንድሮው የሐጂ ጉዞ ከኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሁጃጆች የተሳተፉበት መሆኑን ገልጸዋል።

የአረፋ በዓልን ሕዝበ ሙስሊሙ ሰላሙን በማጽናት፣ በአንድነት፣ በመረዳዳትና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሊያሳልፉ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ዋና ፀሐፊ ሸህ ሀሚድ ሙሳ በበኩላቸው÷ዕለቱ ከሰማይ ወደ መሬት የወረዱት አደምና ሐዋ ከመጠፋፋት በኋላ በሳዑዲ ዓረቢያ አረፋ ተራራ የተገናኙበትን ክስተት እና ከረመዳን ጾም ቆጥሎ የሚፈጸም ኢስላማዊ ስርዓት ነው ብለዋል።

ሐጂ ማለት ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ሁጃጆች ያለምንም ልዩነት ዱዓ እያደረጉ የአደም ልጅነታቸውን ብቻ የሚያስምሰክሩበት የመዳን ዕለት እንደሆነ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች ይከበራል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.