ከከሸፈው አመፅ በኋላ የዋግነሩ መሪ ቤላሩስ መግባታቸው ተነገረ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የዋግነር ቅጥረኛ ወታደራዊ ኃይል ኩባንያ መሥራች እና መሪ ኤቭጄኒ ፕሪጎዢን ቤላሩስ መግባታቸውን የሀገሪቷ ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ገለጹ፡፡
ቅዳሜ ዕለት ከከሸፈው አመፅ በኋላ የአማፂያኑ መሪ ቤላሩስ የገቡት ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ትናንት ምሽት ላይ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት የቀረቡላቸውን የሠላም አማራጮች ተከትሎ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በአውሮፕላን ቤላሩስ ዋና ከተማ ሚኒስክ መግባታቸውን በሀገሪቷ ብሔራዊ ዜና ማሰራጫ ያስታወቁት የሀገሪቷ ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ናቸው፡፡
የኩባንያው መሥራች ኤቭጄኒ ፕሪጎዢን ለወታደራዊ ኃይሎቻቸው ከሩሲያ ለቀው እንዲወጡ ጥሪ እንዳስተላለፉም ነው ተነገረው፡፡
ፕሬዚዳንት ፑቲን ካቀረቧቸው አማራጮች መካከል ÷ ከሀገሪቷ መከላከያ ሚኒስቴር ጋር ውል በመፈራረም እንዲቀላቀሉ ፣ በሀገሪቷ በሚገኙ ሌሎች ሕጋዊ የደኅንነት ኤጀንሲዎች ውስጥ እንዲሠሩ ፣ በሠላም ወደ ቤተሰቦቻቸው በመሄድ የግል ሕይወታቸውን እንዲመሩ ወይም ወደ ጎረቤት ሀገር ቤላሩስ ማቅናት የሚሉት አማራጮች ቀርበውላቸው እንደነበር አር ቲ ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ÷ አብዛኞቹ የዋግነር ኩባንያ ወታደሮች እና የጦር አዛዦች ለሕዝባቸው እና ለሀገራቸው ለመሞት ቁርጠኛ የሆኑ አርበኞች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በቅዳሜው አመፅ የተሳተፉ የዋግነር ወታደሮች ግን እንደተሳሳቱና የአንዳንድ አስተባባሪዎቻቸው መጠቀሚያ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
አጋጣሚው ለሀገራቸው በጋራ ሲዋደቁ የነበሩትን ወንድማማቾች እርስ በእርስ ያጫረሰ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡
እስከ መጨረሻዋ ሠዓት ድረስ ከሀገራቸው ጎን በመቆም በወንድማማቾች መካከል ደም መፋሰስ እንዳይኖር የፀኑትን የዋግነር ወታደሮች እና አዛዦችም አመስግነዋል፡፡
አመጹ መቋጫ ያገኘው ሩሲያ በቤላሩሱ ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ አደራዳሪነት ከወታደር ቀጣሪው ኩባንያ ዋግነር አመራር ኤቭጄኒ ፕሪጎዢን ጋር መግባባት ላይ በመድረሷ መሆኑን አር ቲ ዘግቧል፡፡
በስምምነቱ መሠረት በኤቭጄኒ ፕሪጎዢንም ሆነ በአመጹ የተሳተፉት ወታሮቹ ላይ ያለ የወንጀል ክስ ይቋረጣል፤ አዲስ ክስም አይመሠረትም ተብሏል፡፡
በዚህም መሠረት ነው የዋግነር ወታደራዊ ኩባንያ መሥራች እና መሪ ኤቭጄኒ ፕሪጎዢን እና ጥሪ የቀረበላቸው ወታደሮቻቸው ቤላሩስ መግባትን በመምረጥ ወደዚያው ያቀኑት፡፡
የሩሲያ መንግስት ከፈረንጆቹ 2022 እስከ 2023 ለዋግነር ወታደራዊ ኩባንያ ተልዕኮ ማስፈፀሚያ ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ ማውጣቱን የሩሲያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።