Fana: At a Speed of Life!

የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ለኢድ አል አድሀ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ነገ የሚከበረውን 1 ሺህ 444ኛው የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ 1 ሺህ 444ኛውን የኢድ አል አድሀ (አረፋ ) በዓል አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም÷በዓሉ በምዕመናን ዘንድ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ጠቅሰው የአንድነትና የአብሮነት እሴቶቻችን በጉልህ የሚንጸባረቁበት ነው ብለዋል።

በዓሉ ሙስሊሞች ተሰባስበው ሀይማኖታዊ ግዴታቸውን የሚወጡበት ብቻ ሳይሆን የቦታ ርቀት፣ ባህል፣ቋንቋና ቀለም ሳይገድባቸው አንድ ሆነው ወንድማማችነታቸውን በተግባር የሚያሳዩበት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

አረፋ አቅመ ደካማውም፣ ባለጸጋውም እኩል እንዲያሳልፈው እምነቱ ግዳጅ ያስቀምጣል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በተለይም ደግሞ በእምነቱ እሳቤ መሰረት እርድ በሚፈጸምበት ወቅት ለተቸገሩ ወገኖች የሚሰጠው ምጽዋት ብዙዎችን የሚያኮራ ድንቅ እሴት በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።

ለእስልምና እምነት ተከታዮች በዓሉ የሰላም፣ የጤና የመተሳሰብ እና የአንድነት በዓል እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ መሃመድ ለኢድ አል አደሃ (አረፋ) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም÷የአረፋ በዓል በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ትርጉም ያለው ፣ የደስታ፣ የእዝነት፣ የርህራሄ፣ የመተሳሰብና የአንድነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

“በዓሉን ያለው ለሌው በማካፈል እንዲሁም አቅመ ደካሞችን በመርዳት በአብሮነት በመልካም እሳቤ ልናሳልፈው ይገባልም”ብለዋል፡፡

ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮችም በዓሉ የሰላምና የደስታ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

እንዲሁም÷ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺህ 444ኛው ኢድ- አል አደሃ (ዓረፋ) በዓል በሠላም አደረሳችሁ ብለዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በዓሉን ስናከብር ካለን ላይ በማካፈል ኢትዮጵያዊ የመተሳሰብ ባህላችንን በማጠናከር ሊሆን ይገባልም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በበዓሉ ህዝበ ሙስሊሙ በኢትዮጵያዊ የመተሳሰብ እና የመረዳዳት ባህል የተቸገሩትን በመርዳትና ከሌሎች የእምነቱ ተከታይ ወንድምና እህት ጋር ማዕድ በመጋራት ማክበር ይገባል ብለዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሃጂ አወል አርባ የኢድ አልድሃ በዓልን በማስመልከት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በመልዕክታቸው÷በዓሉ ኡድሂያ እርድ የሚፈፀምበት በመሆኑ በዓሉን ስናከብር ጎረቤቶችን የተቸገሩትን በማስታወስ ከምንጊዜውም በላይ ማህበራዊ ግንኙነት በማጠናከር መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

የዘንድሮው አረፋ በዓል ኢትዮጵያ የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ተግባራዊ በማድረግ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በተግባር ያሳየችት፤ ነገን ዛሬ እንትከል ሁለተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ በሀገር አቀፍ ደረጃ በክልላች የጀመርንበት ኢትዮጵያ በፓሪሱ የፋይናንስ ጉባኤ ላይ ተሳትፋ በመድረኩ የተሻለ ተደማጭነት ያገኘችበት ወቅት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል።

በተመሳሳይ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)÷የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓለም መቻቻል፣ መከባበር፣ መረዳዳት፣ ተካፍሎ የመብላትና በማህበራዊ ህይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ልዩነቶችን በጋራ የመፍታት እሴት ጎልቶ የሚታይበት በዓል ነው ብለዋል።

ልዩነቶችን በጋራ የመፍታትና ሰላምን የማጽናት ኃላፊነት የሁሉም ኃይማኖት አባቶችና ተቋማት ቀዳሚ አስተምህሮ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ይሁን እንጂ ዘላቂ ሰላም የሚጸናው በሁሉም ዜጎች የጋራ ጥረት በመሆኑ ሁላችንም ለሰላም መስፈን ባለቤቶች መሆን አለብን ነው ያሉት።

ሕዝበ ሙስሊሙም በዓሉን ሲያከብር ኃይማኖታዊ ህግጋቱ በሚያዘው መሰረት ለሰላም ዘብ በመቆም፣ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት፣ በመደጋገፍና በአንድነት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

ለእምነቱ ተከታዮችም 1ሺ 444ኛው የኢድ አል አድሀ በዓል የሰላም፣ የመተሳሰብና የአንድነት እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.