አቶ ደመቀ መኮንን የደቡብ – ለደቡብ የትብብር ማዕቀፍ እንዲጠናከር በቅንጅት እንዲሠራ አሳሰቡ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የደቡብ – ለደቡብ የትብብር ማዕቀፍ እንዲጠናከር አባል ሀገራቱ በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የትምህርት ትብብር ድርጅት ልዩ ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
የወቅቱ የጠቅላላ ጉባዔው ፕሬዚዳንት አቶ ደመቀ መኮንን÷ የደቡብ – ለደቡብ ትብብር ማዕቀፍ እና የባለ ብዙ ወገን ትብብር ቁልፍ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ አባል ሀገራቱ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
ጠቅላላ ጉባዔው በዛሬ ውሎው በድርጅቱ ሥም አወጣጥ፣ በሚመራባቸው ደንቦች እና አሠራሮች ላይ ውይይት አድርጓል።
በዚህም ቀደም ሲል በእንግሊዝኛ ቋንቋ (Organization Of Education Cooperation) ወይም ወደ አማርኛ ሲመለስ “የትምህርት ትብብር ድርጅት” እየተባለ ሲጠራበት የነበረው ሥያሜ ቀርቶ (Organization for Southern Cooperation) ወይም “የደቡብ ንፍቀ-ክበብ ሀገራት ትብብር ድርጅት በሚል ሥያሜ እንዲቀየር በጠቅላላ ጉባዔው ተወስኗል።
የትምህርት ትብብር ድርጅት ዋና ፀሐፊ ሼክ መንሱር ቢን ሙሠላም÷ ድርጅቱ እንዲጠናከር እና እስትራቴጂያዊ ግቦቹ እንዲሳኩ በጉባዔው ተሳታፊ የሆኑ አባል ሀገራት ያደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
ጉባዔው ለሁለት ቀናት በሚኒስትሮች ደረጃ የተካሄደ ሲሆን÷ በቀሪዎቹ ቀናት የድርጅቱ አባል ሀገራት መሪዎች ምክክር ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ድርጅቱ ሚዛናዊ፣ አካታች እና ሁሉን አቀፍ የትምህርት ሥርዓት በመዘርጋት በእኩልነት፣ ፍትሐዊነት እና አጋርነት ላይ የተመሠረተ ልማት ማሳካትን ያለመ ስለመሆኑም ተጠቁሟል፡፡
አቶ ደመቀ መኮንን የፕሬዚዳንትነት ጊዜያቸው በመጠናቀቁ ለቀጣዩ የድርጅቱ ፕሬዚዳንት ለኮሞሮሱ አዛሊ አሱማኒ አስተላልፈዋል።