Fana: At a Speed of Life!

12 ሺህ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የመስሪያ ቦታ ቁልፍ ተረከቡ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለ12 ሺህ የከተማዋ ነዋሪዎች የመስሪያ ቦታ (ሼዶች) ቁልፍ አስረከበ፡፡

አስተዳደሩ የመስሪያ ቦታ ቁልፍ ያስረከበው÷ በ2 ሺህ 389 ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ 12 ሺህ የመዲናዋ ነዋሪዎች መሆኑን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ ከ2 ወራት በፊት ከከተማዋ ሴቶችና ወጣቶች ጋር በተደረጉ ውይይቶች ከመስሪያ ቦታና የስራ ዕድል ፈጣራ ጋር በተያያዘ ኢ-ፍትሐዊነት እንዳለ መነሳቱን አስታውሰዋል፡፡

በመሆኑም አጣርተን ችግሮች መኖራቸውን በማረጋገጥ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ባልተወጡና የአሰራር ጥሰት በፈፀሙ አመራሮችና ባለሙያዎች ላይ ተገቢ የእርምት እርምጃ ወስደናል ነው ያሉት፡፡

በዚሁ መሠረት በ2 ሺህ 389 ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ 12 ሺህ የከተማችን ነዋሪዎች የመስሪያ ቦታ አስረክበናል ብለዋል።

በሸራ ቤት ሲነግዱ የነበሩ የመስሪያ ቦታ የሚገባቸው አካል ጉዳተኞች እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ነዋሪዎችን በማረጋገጥ የመስሪያ ቦታ ተሰጥቷቸው ሥራዎቻቸውን በሕጋዊ መንገድ እንዲቀጥሉ ስለመደረጉም አስረድተዋል።

ዛሬ የመስሪያ ቦታ የተሰጣቸው አካል ጉዳተኞች፣ ወጣቶችና ሴቶች የመስሪያ ቦታ ማግኘት በራሱ ግብ አለመሆኑን ተገንዝበው÷ ተግተው በመስራት ለሌሎች የስራ እድል በመፍጠር ራሳቸውን እንዲለውጡ አሳስበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.