Fana: At a Speed of Life!

ከ838 ግራም በላይ ወርቅ ሲያሸሹና ህገወጥ ጦር መሣሪያ ይዘው የተገኙ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያና በጋምቤላ ክልሎች ከ838 ግራም በላይ የወርቅ ማዕድን ሲያሸሹና ህገወጥ ጦር መሣሪያ ይዘው ተገኝተዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታውቋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልና በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ 20 ክላሽንኮቭ ከ934 መሰል ጥይቶች ጋር፣ 8 ሽጉጥ ከ54 መሰል ጥይቶች ጋር፣ ሁለት ኤፍ ዋን ቦንቦች እና አንድ ጂ ፒ ኤስ መያዛቸው ተገልጿል፡፡

ከዚህ ባለፈም 172 የተለያዩ የወርቅ ጌጣጌጦች፣ ከ838 ግራም በላይ የወርቅ ማዕድን፣ 7 የወርቅ ማቅለጫ ማሽኖች፣ 10 የወርቅ ሚዛን፣ ከ1 ሚሊየን 653 ሺህ ብር በላይ በአሶሳ ዞን ጉሙሩክ የፍተሻ ጣቢያ መያዛቸው ተጠቁሟል ።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በሕገ-ወጥ መንገድ የወርቅ ማዕድን በማሸሽ ለግል ጥቅማቸው ለማዋል ሲሉ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ከህብረተሰቡ ባገኘው መረጃ መሠረት አሶሳ ዞን ኩምሩክ የፍተሻ ጣቢያ ባደረገው ፍተሻ መሆኑ ታውቋል።

በተጨማሪም በጣቢያው በተካሄደው ፍተሻ 20 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ፤ ከ934 መሰል ጥይቶች ጋር እና ስምንት የተለያዩ ሽጉጦች ከ54 መሰል ጥይቶች ጋር፣ ሁለት ቦንቦች እና አንድ ጂፒኤስ መያዛቸው ተመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያን በመጣስ በግለሰብ ደረጃ ከ1 ሚሊየን 653 ሺህ ብር በላይ ይዘው ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳዩ በምርመራ እየተጣራ መሆኑ ተገልጿል።

ህብረተሰቡ በመሰል የወንጀል ድርጊቶች የተሰማሩ ግለሰቦችና ቡድኖችን በማጋለጥ አሳልፎ ለፀጥታ አካላት በመስጠት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ግብረ-ኃይሉ ጥሪ አቅርቧል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.