Fana: At a Speed of Life!

በኢንቨስትመንት ዙሪያ በኮርፖሬሽኑ የጀመርናቸውን ስራዎች አጠናክረን እንቀጥላለን – በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢንቨስትመንት እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር የጀመርናቸውን ስራዎች አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩኣን ገለጹ፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ በኢትዮጵያ ከቻይና አምባሳደር ጋር ተወያይተዋል።

አቶ አክሊሉ ታደሰ በውውይቱ ወቅት÷በኮርፖሬሽኑ ስለሚተዳደሩ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ወቅታዊ መረጃዎችን በማቅረብ ቻይናውያን ባለሀብቶች ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮችና የነፃ ንግድ ቀጠና ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

መንግስት ለውጪና ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በፖሊሲና በማበረታቻዎች ያደረገውንም ማሻሻያም በዝርዝር አቅርበዋል።

ቻይናና ኢትዮጵያ ጠንካራ ወዳጅነትና ትብብር እንዳላቸው ጠቅሰው÷ይህም ወንድማማችነት በኢኮኖሚና በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልፀዋል።

አምባሳደር ዣኦ ዢዩኣን በበኩላቸው÷ ኮርፖሬሽኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀገሪቷ የጀመረችውን የኢንዱስትሪያላይዜሽን ጉዞ እውን ለማድረግ የሚያስችል በቂ ቁመና ላይ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከኮርፖሬሽኑ ጋር ከኢንቨስትመንት ባሻገር በትምህርትና ስልጠና በትብብር ለመስራት ኤምባሲያቸው ሙሉ ዝግጅት እንዳለውም መግለጻቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

በውይይቱ ከኢንቨስትመንት፣ከሰዉ ሀይል ስልጠና እንዲሁም ከትምህርት እድል በተጨማሪም በሌሎችም የትብብር ማዕቀፎች ላይ አብሮ ለመስራት ከስምምነት ላይ ተደርሷል ተብሏል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.