Fana: At a Speed of Life!

ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።

አቶ ኦርዲን እና ካቢኔያቸው በጉብኝታቸው÷ በ175 ሚሊየን ብር ወጪ እየተገነባ ያለውን ባለ 4 ወለል የእሳት እና ድንገተኛ አደጋ መከላከል ህንጻ ፕሮጀክት ተመልክተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በክልሉ እና አካባቢው ለሚያጋጥሙ አደጋዎች ፈጥኖ ምላሽ መስጠት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን ÷ አመራሩ የተጀመሩ የካፒታል ፕሮጀክቶችን ከፍጻሜ ለማድረስ በሃላፊነት ሊሰራ እንደሚገባም ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የከተማ ተቋማዊ እና መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ፈቲ ረመዳን በበኩላቸው÷የእሳት እና ድንገተኛ አደጋ መከላከል ህንጻ ፕሮጀክት ግንባታ 96 በመቶ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ በ18 ወራት ውስጥ ስራውን ለማጠናቀቅ ውል ተገብቶ እንደነበር ጠቅሰው÷ ሆኖም በ11 ወራት ውስጥ እየተገባደደ እንደሚገኝና በተያዘው ወር መጨረሻ ለማጠናቀቅ መታቀዱን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል በሐረር ከተማ በ42 ሚሊየን ብር በጀት ሲካሄድ የቆየው የ17 ኪሎ ሜትር የጀጎል ውስጥ ለውስጥ መንገድ የኤሌክትሪክ መብራት መስመር ዝርጋታ ተጠናቆ በርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ ተመርቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.