የወረዳ ዋና ስራ አስፈጻሚና ምክትላቸው የመስሪያ ቦታ ለመስጠት ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ ተያዙ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ዋና ስራ አስፈጻሚና ምክትላቸው በመስሪያ ቦታ አሰጣጥ ተደራድረው የሙስና ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።
የጉለሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ረ/ኮሚሽነር ፋሲካ ፈንታ እንደገለጹት÷በክፍለ ከተማው ወረዳ 3 ከስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ብሎክን መሰረት በማድረግ የተፈጠረ የስራ እድል ላይ ከተጠቃሚ ወላጅ ጋር የተሻለ የመስሪያ ቦታ እናሰጣለን በማለት የተጠቃሚዋን አባት ብር ካልሰጠኸን ልጅህን የስራ እድል አይፈጠርላትም በማለት ወላጅ አባቷን በማስፈራራት ልዩ ስሙ 6 ኪሎ አከባቢ 50 ሺህ ብር ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል።
የወረዳ 3 ዋና ስራ አስፈፃሚ አያናው አስራት እንዲሁም ምክትል ስራ አስፈጻሚና የስራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ እዮብ አፈወርቅ ብር ሲቀበሉ በጸጥታ ሃይሎች እጅ ከፍንጅ ተይዘው ተጨማሪ ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል ተብሏል።
የክ/ከተማው ፖሊስ መምሪያ ይህንን አይነት ፍፁም ተገቢ ያልሆነ ተግባር ኮንነው ባስተላለፉት መልዕክት÷
የከተማዋ ነዋሪ በየትኛውም የመንግስት ተቋም ለሚሰጡ አገልግሎቶች ሙስና ለመቀበል የሚጠይቁና የሚቀበሉ ማናቸውንም አካላት በመጠቆም ተባባሪ እንዲሆን ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ነዋሪው በዚህ አጋጣሚ መሰል ነገር በሚገጥመው ወቅት ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት ለሕግ አስከባሪ አካላት የተለመደ ትበብሩን እንዲያደርግም ጥሪ መቅረቡን የከመዋ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡