Fana: At a Speed of Life!

ዐቃቤ ሕግ በሽብር ወንጀል በተጠረጠሩ 20 ግለሰቦች ላይ የሽብር ወንጀል ክስ መሰረተ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁ እና የድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ በሽብር ወንጀል በተጠረጠሩ 20 ግለሰቦች ላይ የሽብር ወንጀል ክስ መስርቷል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ-ሽብርና የሕገመንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በዐቃቤ ሕግ የተመሰረተውን የክስ ዝርዝር ለ16 ተከሳሾች እንዲደርስ አድርጓል።

ቀሪ 5 ተከሳሾች ግን የቀረበብን ክስ በማንነታችን ምክንያት በመሆኑ አንቀበልም በማለት በፈቃዳቸው የክስ ዝርዝሩን ሳይቀበሉ ቀርተዋል።

የክስ ዝርዝሩ ለተከሳሾች እንዲደርስ ከተደረገ በኋላ የተከሳሽ ጠበቆች በኩል ተከሳሾቹ ባሳለፍነው ዓርብ በነበረ ጊዜ ቀጠሮ ለዐቃቤ ሕግ በተሰጠ የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ ውስጥ ክሱን ባለማቅረቡ ምክንያት ለተከሳሾቹ በጊዜ ቀጠሮ ችሎት የዋስትና መብት ተከብሮላቸው ዋስትና ተከፍሎ ነገር ግን ከስር መፈታት ሳይችሉ መቅረታቸውን ጠቅሰው አቤቱታ አቅርበዋል።

በከሳሽ ዐቃቤ ሕግ በኩል በዕለቱ ክስ መክፈቱን ጠቅሶ የክስ ዝርዝሩ ከነማስረጃው ባጠቃላይ 18 ሽህ መሆኑን ተከትሎ በፍ/ቤቱ ሬጅስትራል በኩል እያንዳንዱን ማስረጃ ሳታመሳክሩ እንዳትከፍቱ ተብለን ታዝዘናል ተብሎ በመገለጹን ጠቅሶ በሱ በኩል ግን በዕለቱ ክስ መመስረቱን አስረድቷል።

በወቅቱ ክስ መስርተናል ያለው ዐቃቤ ሕግ በፍርድ ቤቱ ሬጅስትራል ምክንያት ማስረጃ ተመሳክሮ ባለመጠናቀቁ መነሻ ተጨማሪ 3 ቀን እንዲሰጠው መጠየቁንና ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ጥያቄውን ሳይቀበል በመቅረት ለተከሳሾቹ ዋስትና መፍቀዱን ገልጿል።

ይሁንና ይህን የተፈቀደው ዋስትና ተከትሎ ወደ ጠቅላይ ፍ/ቤት በመሄድ በዕለቱ ይግባኝ በመጠየቅ እና ይግባኙ ያስቀርባል ተብሎ በሰኔ 20 ቀን ደግሞ የእስር ፍርድ ቤት የሰጠው ዋስትና ውሳኔ ላይ እግድ መጣሉን በሰጠው መልስ ላይ በማብራራት ተከሳሾቹ በስር እንዲቆዩ የተደረገበት አካሄድ ሕጋዊ ነው ”እኛ ግዴታችንን ተወጥተናል ”በማለት ዐቃቤ ሕግ ተከራክሯል።

በዚህ ጊዜ በተከሳሽ ጠበቆች በኩል ይግባኝ መባሉን እንደማያውቁና በጉዳዩ ላይ አለመሰየማቸውን እንዲሁም ስለ እግድ መሰጠቱ እስከ ሰኔ 20 ድረስ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ጠቅሰው በዐቃቤ ሕግ ቸልተኝነት ተከሳሾቹ ያለአግባብ በእስር እንዲቆዩ እና እንዲጉላሉ ተደርገዋል በማለት ተከራክረዋል።

በተቻለ መጠን በሁለቱም ተከራካሪ አካላት በኩል ለችሎቱ የሚመጥኑ ቃላቶች እንዲሰነዘሩ ሀሳብ ተሰጥቷል፡፡

በሌላ በኩል ተከሳሾቹ ከግንቦት 18 ቀን በፊት ለ24 ቀናት በኦሮሚያ ክልል ገላን እስር ቤት ደርሶብናል ያሉትን ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በዝርዝር ጠቅሰው እያንዳንዳቸው ለችሎቱ አቅርበዋል።

የስነ-ልቦና እና አካላዊ ጥቃት እንዲደርስብን አድርገዋል ያሏቸውን የፀጥታ ተቋማት መርማሪዎችና ኃላፊዎችን ስም ገልፀው በጠቀሷቸው  የፀጥታ አካላት ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል፤የችሎቱ ዳኞች በገላን ታስረን ነበር ያሉበትን ቦታ እንዲመለከቱላቸውም የጠየቁ ተከሳሾች ነበሩ።

በተጨማሪም ተከሳሾቹ  ከዚህ በፊት  በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እንዲጣራላቸው ያመለከቱት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማጣራት ውጤቱ ምን ደረጃ ላይ ደረሰ ሲሉ ጠይቀዋል።

እንዲሁም 3 ተከሳሾች ባጋጠማቸው የጤና ዕክል ምክንያት በሚፈልጉት ሕክምና ተቋም ለመታከም እንዲችሉ እንዲታዘዝላቸው አመልክተዋል።

ውክልና መስጠት የሚፈልጉ ሌሎች 3 ተከሳሾች እና በመስሪያ ቤቱ ንብረት ርክክብ ለማድረግ የሚፈልግ 14ኛ ተከሳሽ በአጃቢ ጉዳያቸውን መፈጸም እንዲችሉ እንዲፈቀድላቸው ጠይቃዋል።

በተጨማሪም ሌላ አንድ ተከሳሽ ከዚህ በፊት ወደ አሜሪካ ለመሄድ ዲቪ ሞልቶ እንደደረሰው ጠቅሶ ፓስፖርት ለማደስና ወደ አሜሪካ ኤንባሲ ሄዶ ጉዳይ ለመፈጸም እንዲችል እንዲታዘዝለት ችሎቱን ጠይቋል።

ይህን አቤቱታን ተከትሎ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ የሚቀርቡ አቤቱታዎች ማለትም ህክምና በግል ለማድረግ ለምን አስፈለገ የሚሉ ዝርዝር ነጥቦች ሰው ኃይል ከመንግስት ወጪ፣ ከተሽከርካሪ አንጻር ግምት ውስጥ አስገብቶ  ፍርድ ቤቱ ሊመለከት ይገባል ሲል ተከራክሯል።

የተከሳሽ ጠበቆች ÷ ዐቃቤ ሕግ ችሎቱን በሚመራ መልኩ አስተያየት መስጠት የለበትም በማለት የመቃወሚያ መከራከሪያ ነጥብ አንስተዋል።

ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ  የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በሚመለከት ከዚህ በፊት ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ትዕዛዝ የሰጠው ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በኩል ክትትሉ ሊቀጥል ይገባል እንጂ በዚህኛው ችሎት ሊቀርብ አይገባም የሚል ጥያቄ አንስቷል።

ዐቃቤ ሕግ  የተከሳሾቹ ማንነት ሳያረጋግጥ ቀድሞ በቀረቡ አቤቱታዎች ላይ የስነስርዓታዊ አካሄዱን ባልተከተለ መልኩ ፍርድ ቤቱ  ትዕዛዝ ሊሰጥበት አይገባም የሚል መከራከሪያ አንስቷል።

በተጨማሪም ዐቃቤ ሕግ ከ2012 ዓ/ም አዋጅ ወጥቶ ተግባራዊ ከተደረገ ጀምሮ በዚህ ስርዓት ያለፉ ትልልቅና ተሰሚነት ያላቸው ታዋቂ ሰዎች በምርመራ ወቅት ስለነበረው የሰብዓዊ መብት አያያዝ አመስግነው ያለፉት በአደባባይ ጥሰት ተፈጽሟል ለማለት ያስቸግረናል በሚል ዐቃቤ ሕግ የሰጠውን አስተያየት ተከትሎ በተከሳሽ ጠበቆችና በተከሳሾች በኩል ተቃውሞ አስነስቷል።

ጠበቆቹ  ዐቃቤ ሕግ ለተከሳሶች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተከትሎ እንዲጣራ ሊተባበርና እገዛ ሊያደርግ ሲገባ ስነልቦናቸውን በሚጓዳ መልኩ  አስተያየት የሰጠበት መንገድ ተገቢ አይደለም የሚሉ ነጥቦችን አንስተዋል።

በፍርድ ቤቱ የግራ ዳኛ  በዐቃቤ ሕግ የሚሰጡ አስተያየቶች ለስላሳና የተከሳሾችን ስነልቦና ታሳቢ ያደረጉ ቢሆኑ የሚሉ ሀሳቦችን ሰንዝረዋል።

የተከሳሽ ጠበቆች የተከሳሾች የጤና ጉዳይ አፋጣኝ መፍትሄ የሚያስፈልገው መሆኑን ጠቅሰው÷ ማንነታቸው እስኪረጋገጥ ተብሎ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም በማለት ተከራክረዋል።

ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ ያሉበት የፌዴራል ፖሊስ ከእስረኞች ቁጥር ከፍ ማለት ጋር ተያይዞ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሶ ተከሳሾቹ ዋስትና ላይ ክርክር እስኪደረግ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ጠይቋል።

በተከሳሽ ጠበቆች በኩል ግን የዐቃቤ ሕግ ፖሊስና የሰብዓዊ መብት ተቋማትን ወክሎ አስተያየት መስጠቱ ተገቢ አይደለም በማለት ተከሳሾቹ  ያሉበት ማረፊያ  እንዲቆዩ ጠይቀዋል።

በዚህ መልኩ ችሎቱ ከረፋድ 4 ሰዓት እስከ ከሰዓት 10 ሰዓት ድረስ ያለማቋረጥ የቀጠለ ሰፊ ክርክር ተከታትሏል።

በፍርድ ቤቱ በመረጡት የህክምና ተቋም ህክምና ለማግኘት፣ ውክልና ለመስጠት እንዲሁም የመስሪያ ቤት ንብረት ርክክብ ለማድረግ ያመለከቱ ተከሳሾችን በሚመለከት ተገቢው እጀባ ተደርጎላቸው እንዲፈጸምላቸው ለፖሊስ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

ሌሎችን አቤቱታዎችና ክርክር የተደረገባቸውን ጉዳዮች ላይ ፍርድ ቤቱ መርምሮ ተገቢውን ትዕዛዝ ለመስጠት ለሰኔ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በአጠቃላይ ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ሀ /ለ፣ አንቀጽ 38 እንዲሁም የሽብር አዋጅ 1176/2012 አንቀጽ 6/2 ተላልፈዋል የሚል የሽብር ወንጀል ክስ  አቅርቧል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.