ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) የዜጎችን ማህበራዊ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚሰሩ ተግባራት እንዲጠናከሩ አሳሰቡ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በክረምት በጎ ፈቃድ አግልግሎት የዜጎችን ማህበራዊ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚሰሩ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር አሳሰቡ፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ ” በሚል መሪ ሐሳብ ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄድ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ክልላዊ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።
ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በክረምት የበጎ ፈቃድ ተግባር ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ከመንግሥት ጎን በመሆን የዜጎችን ማህበራዊ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዲጠናከር ጠይቀዋል፡፡
በ2014 የክረምት በጎ ፈቃድ የተሰራው ተግባር የሚደነቅ ነው ማለታቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በ2015 ክረምት በጎ ፈቃድ በ13 መስኮች 601 ሺህ 303 በጎ ፋቃደኞችን በማሳተፍ÷ 1 ሚሊየን 162 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱ ተገልጿል፡፡
በ2014 የክረምት ወቅት 491 ሺህ 70 በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ 954 ሺህ 469 የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተጠቁሟል፡፡