የተፈጠረው ሰላም በፅኑ መሰረት ላይ እንዲቆም በጋራ መስራት ያስፈልጋል – የኦሮሞ ብሔረሰብ እና የሰሜን ሸዋ ዞን አመራሮች
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአካባቢው የተፈጠረውን ሰላም በፅኑ መሰረት ላይ እንዲቆም በጋራ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ እና የሰሜን ሸዋ ዞን አመራሮች ገለጹ፡፡
የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን እና ሰሜን ሸዋ ዞን አመራሮች በሁለቱ ዞኖች መካከል ያለውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ያለመ ውይይት አካሂደዋል፡፡
የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ከድር ዓሊ÷ ከዚህ በፊት በሁለቱ ዞኖች መካከል ሰላም ሰፍኖ እንደነበር እና በተለያየ ጊዜ ደግሞ በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት አለመግባባቶች መፈጠራቸውን አስታውሰዋል፡፡
በዚህም በተደጋጋሚ በተደረጉ ውይይቶች አንፃራዊ ሰላም መስፍኑን አስገንዝበው÷ የተፈጠረው ሰላም በፅኑ መሰረት ላይ እንዲቆም በጋራ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
በሁለቱ ዞኖች መካከል የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስም በትኩረት መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የአጣዬ ከተማ ከንቲባ አሳልፍ ደርቤ በበኩላቸው÷ በአካባቢው የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ማለታቸውን የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡