በኢንዱስትሪ ፓርኮች በተፈጠረ የገበያ ትስስር ከ300 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመላው ኢትዮጵያ በተገነቡ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተፈጠረ የገበያ ትስስር ከ300 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ፡
የኮርፖሬሽኑ የማርኬቲንግና ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘመን ጁነዲን ÷በመላው ሀገሪቱ በተገነቡት የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች የግብርና ምርቶቻቸውን በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ላሉ አምራቾች እንዲያቀርቡ በማድረግ ሰፊና ዘላቂ የገበያ ትስስር በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በገበያ ትስስሩ ከ 15 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአቮካዶ ዘይት ምርት በማምረት ለተሰማራ ኩባንያ የአቮካዶ ፍራፍሬ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡
በደብረ ብርሃን እና ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ ለቢራ አምራች ካምፓኒዎች ብቅል የማቅረብ ስራ ለሚሰሩ አምራቾች የቢራ ገብስ በማቅረብ በኩል ከ280 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገቡ ስራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኙ ነው የገለጹት፡፡
በቅርቡም በአፋር አካባቢ ያለውን የግመል ወተት በግብዓትነት የሚጠቀም ካምፓኒ በሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲሁም አማራ ክልል አካባቢ ያለውን የበቆሎ ምርት በግብዓትነት የሚጠቀም አምራችም እንዲሁ በባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብተው ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ፈጽመው ግንባታ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተልባ እግርን በግብዓትነት የሚጠቀም ካምፓኒ ጋር የገበያ ትስስር ስራዎች ለመስራት የዘር ብዜትና የምርምር ስራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ኃላፊው÷ በቀጣይም የዘር ብዜቱን ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት በስፋት ወደ ምርት እንዲገቡ የማድረግ ስራዎች እንደሚሰሩ አብራርተዋል፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኮች በአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በፋርማሲዩቲካል ዘርፎች ተሰማርተው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በተለይም ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ ያለው የኢንቨስትመንት ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ መነቃቃቱንና የባለሃብቶች ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎትም በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
በኮርፖሬሽኑ አሁን ላይ 11 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሙሉ በሙሉ በስራ ላይ የሚገኙ ሲሆን÷ የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክን ወደ ስራ ለመመለስም የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ እንደቆዩ መናገራቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡