Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በ62 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነቡ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተመረቁ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በ62 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነቡ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀዋል።

ፕሮጀክቶቹን የመረቁት በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር)ና ሌሎች የክልሉ የስራ ኃላፊዎች ናቸው።

በሰሜን ሸዋ ዞን አሌልቱ ወረዳ ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል በሶላር ሀይል የሚሰራ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትና ድልድይ ይገኝበታል።

በአጠቃላይ በወረዳው 19 የተለያዩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት የበቁ ሲሆን÷ ዛሬ የተመረቀው የንጹህ መጠጥ ፕሮጀክት 49 ሚሊየን ብር ወጪ እንደተደረገበትም ታውቋል።

በተጨማሪም በወረዳው ቦርቴ ወንዝ ላይ በ13 ሚሊየን ብር የተገነባው ድልድይም ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።

በዚሁ ጊዜ በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ /ር) የፕሮጀክቶቹ ለአገልግሎት መብቃት የህዝቡ የረጅም ጊዜ ትግል ውጤት እያስገኘ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል።

የዚሁ ማሳያ የሆኑ ፕሮጀክቶች በኦሮሚያ ክልል ሁሉም ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች 19 ሺህ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች እየተመረቁ መሆኑን መናራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ከፍያለው አደሬ በበኩላቸው÷ የዞኑ ሕዝብ የተመረቁ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን መንከባከብ እንዳለበት አሳስበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.