ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የጀርመን ጉብኝታቸውን ሰረዙ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በጀርመን ሊያደርጉት የነበረውን ጉብኝት ሰረዙ፡፡
ፕሬዚዳንቱ ጉብኝቱን የሰረዙት በሀገሪቱ በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት መሆኑ ታውቋል፡፡
የጀርመን ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት እንዳስታወቀው÷ኢማኑኤል ማክሮን ከ23 ዓመታት በኋላ በጀርመን የመጀመሪያውን የስራ ጉብኝት ለማድረግ ቀጠሮ ይዘው የነበረ ቢሆንም በፈረንሳይ በተከሰተው አለመረጋጋት ምክንያት ጉብኝታቸው ተሰርዟል፡፡
ማክሮን ቀጠሯቸውን መሰረዛቸውን ለጀርመኑ አቻቸው ፍራንክ ዋልተር ስቴንሚር ማሳወቃቸው የተገለፀ ሲሆን ÷ሊያደርጉት የነበረው የስራ ጉብኝት እንዲራዘምላቸውም ጠይቀዋል፡፡
የጀርመኑ አቻቸው የፕሬዚዳንት ማክሮን ቀጠሮ መሰረዝ መጥፎ አጋጣሚ መሆኑን ገልፀው÷በጎረቤታችን ፈረንሳይ የተፈጠረውን ግጭት እንረዳለን ብለዋል፡፡
ከቀጠሮው መሰረዝ በኋላ ኢማኑኤል ማክሮን በቀጣይ የሚያደርጉት የስራ ጉብኘት ቀን በይፋ አለመታወቁን ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል፡፡
ግጭቱ አንድ የፖሊስ ኦፊሰር የአልጀሪያ ዜግነት ያለውን የ17 ዓመት ወጣት “ትራፊክ ጥሶ አልፏል” በሚል ተኩሶ መግደሉን ተከትሎ በሃገሪቱ አለመረጋጋት መቀስቀሱ የሚታወስ ነው፡፡