Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያና ጅቡቲን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ችግኝ ተከላ ተከናወነ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በይበልጥ ለማጠናከር ያለመ የችግኝ ተከላ ሥነ ሥርዓት በድሬዳዋ ከተማ ተከናውኗል፡፡

በጅቡቲ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሲራጅ ኦማር የተመራ ከ100 በላይ አባላትን ያካተተ የልዑካን ቡድን ዛሬ በድሬዳዋ ከተማ የአረንጓዴ ዐሻራውን አኑሯል፡፡

ሲራጅ ኦማር በድሬዳዋ የተደረገላቸው አቀባበል እንዳስደሰታቸው ገልጸው÷ ይህም የኢትዮጵያን እና የጅቡቲን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጥንካሬ ያሳያል ብለዋል።

በድሬዳዋ ከተማ ተገኝተው አረንጓዴ ዐሻራቸውን በማስቀመጣቸውም መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር÷ ለጅቡቲ 400 ሺህ ችግኞች ለመለገስ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

ዛሬ የተከናወነው የችግኝ ተከላም የኢትዮጵያን እና የጅቡቲን ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያግዝ ነው የገለጹት፡፡

ዛሬ የተከናወነው የችግኝ ተከላ ሥነ ሥርዓት በጅቡቲ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር የሚከናወኑ ሥራዎች አካል መሆኑ ተገልጿል፡፡

የልዑካን ቡድኑ አባላት በድሬዳዋ የነፃ ንግድ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ የጨርቃ ጨርቅና የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካዎችን ጎብኝተዋል።

በአዲስ ታምራት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.