የካንሰር ሕመምን ማዳን የሚያስችል ተሥፋ ሠጪ የጥናት ውጤት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በእስራዔል የቴልአቪቭ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የካንሰር ሕዋሳት መርዛማ ንጥረ-ነገር አመንጭተው ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያጠፉ የሚያስችል ሥልት ይፋ አድርገዋል፡፡
ቴራኖስቲክስ የተሠኘ የምርምር ሥራዎችን የሚያትም መጽሄትይፋ እንዳደረገው ÷ አጥኚዎቹ የዘየዱት ሥልት በመጀመሪያ በካንሰር በታመመ አካል ውስጥ ባለ ባክቴሪያ የሚመረተውን መርዛማ ንጥረ-ነገር ወደ ካንሰር ሕዋሳት እንዲተላለፍ ማድረግ ነበር፡፡
በቀጣይም የካንሰር ሕዋሳቱ ተመሳሳይ መርዛማ ንጥረ ነገሮችን አመንጭተው ራሳቸውን በራሳቸው ሲገሉ መስተዋሉን ሲጂቲ ኤን ዘግቧል፡፡
በጥናቱ ውጤት መሠረትም የካንሰር ሕዋሳቱ የመጥፋት መጠን 60 በመቶ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
የካንሰር ታማሚዎች ላይ የካንሰር ሕዋሳቱን ለመግደል ጥቅም ላይ ሲውል በነበረው የ”ኬሞቴራፒ” ሕክምና÷ በሚለቀቀው ጨረር የታማሚዎች ጤናማ ሕዋሳትም አብረው ስለሚሞቱ የጎንዮሽ ጉዳቶች እንደነበሩት ተጠቁሟል፡፡
አዲሱ የምርምር ውጤትም የቀድሞውን የ”ኬሞቴራፒ ሕክምና” ያስቀራል ተብሎ ከወዲሁ ተሥፋ ተጥሎበታል፡፡